አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የያዘው ግብ አንዲሳካ አባሎቻቸው ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውን የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች አስታወቁ፡፡
ሀገራዊ ምክክሩ የያዘው ግብ ሰፊ በመሆኑ ሂደቱ እንዲሳካ አባሎቻቸው ንቁ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ብሔር አንድነት ፓርቲ ፕሬዚዳንት ዘሪሁን ገብረ እግዚአብሔር ተናግረዋል፡፡
የሀገሪቱን መጻዒ ዕድል ለመወሰንና ቁርሾዎችን በመቅረፍ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን ምክክሩ ወሳኝ መሆኑን አመላክተዋል።
“ሁላችንም ያለችን አንድ ሀገር ስለሆነች ሀገራችንን በሰላምና ብልጽግና ለማቆየት እንዲሁም የሕዝባችንን ሰላምና ደኅንነት ለማስጠበቅ አበክረን መሥራት አለብን” ሲሉ ለኢዜአ ገልጸዋል፡፡
የገዳ ቢሊሱማ ፓርቲ ሊቀመንበር መሳይ አበበ በበኩላቸው÷ የፖለቲካ አለመግባባቶችን በሰለጠነ አስተሳሰብና በመመካከር ለመፍታት ሀገራዊ ምክክሩ ትልቅ አማራጭ ይዞ መምጣቱን ጠቅሰዋል፡፡
ፓርቲያቸውም ሆነ አባሎቻቸው በምክክር ሂደቱ ለመሳተፍ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን እያደረጉ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
የአርጎባ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት ዋና ጸሐፊ መሐመድ ሙሳ÷ ፓርቲያቸው በሚንቀሳቀስባቸው ክልሎች አባላሎቻቸው ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ እየሠራን ነው ብለዋል፡፡
ልዩነቶቻችንን በመነጋገር ለመፍታት ሀገራዊ ምክክሩ ጥሩ ዕድል ይዞልን የመጣ በመሆኑ ልንጠቀምበት ይገባል ሲሉም በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡