የሀገር ውስጥ ዜና

ሚኒስቴሩ ለመቄዶንያ የአረጋዊያንና የአእምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል የሚያደርገውን ድጋፍ እንደሚያጠናክር ገለጸ

By Shambel Mihret

December 31, 2023

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ለመቄዶንያ የአረጋዊያንና የአእምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል የሚያደርገውን ድጋፍ እንደሚያጠናክር አስታወቀ።

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር)ን ጨምሮ የሚኒስቴሩና የተጠሪ ተቋማት ሃላፊዎች የሜቄዶንያን ማዕከል ጎብኝተዋል።

ጉብኝቱ ወቅት የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር)፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሰው ተኮር የሆኑ ስራዎችን በመስራት የዜጎችን ህይወት ለመለወጥ ያስቻሉ ስራዎችን ከመስራት ባለፈ ሁላችንም ይህን ተግባር እንድንሰራ ያተጉናል ብለዋል።

በዛሬው ዕለትም ከትራንስፖርት ወረዳ የብልፅግና ፓርቲ አባላት መዋጮ በመሰብሰብና ተቋማትን በማስተባበር የገንዘብ ድጋፍ መደረጉን ገልፀው፤ የሀገር ባለውለታ የሆኑ አረጋውያንን ለመንከባከብና አቅመ ደካሞችን ለመርዳት የሚሰሩ ስራዎችን ማገዝና ማበርታት የሁሉም ግዴታ መሆኑን አስገንዝበዋል።

የመቄዶንያ ማዕከል ህዝብና ሀገርን እያገለገለ በመሆኑ አመስግነው፤ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ከተጠሪ ተቋማት ጋር በመሆን የ2 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል።

የሚኒስቴሩና የተጠሪ ተቋማት የብልፅግና ፓርቲ አባላት የገንዘብ መዋጮ በማድረግ ያሰባሰቡትን 143 ሺህ 400 ብር እና ከ360 ሜትር በላይ የሆነ ብትን ጨርቅ ድጋፍ አድርገዋል።

ሚኒስቴሩ የመቄዶንያ ማዕከል ለሚያከናውናቸው የግንባታዎች እቃዎችን እስከ 4 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር የማጓጓዣ ወጪ ለመሸፈን እንደሚሰራ የገለጹት ሚኒስትሩ፤ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ለማዕከሉ የሚያደርገውን ድጋፍ እንደሚያጠናክር አረጋግጠዋል።

የመቄዶንያ መስራችና ኃላፊ ቢኒያም በለጠ ስለተደረገው ድጋፍ አመስግነው በቀጣይም በመንግስት እና በኢትዮጵያውያን ድጋፍ ስራውን እየሰራ የሚገኘውን ማዕከል ለማጠናከር የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።