የሀገር ውስጥ ዜና

በጎንደር የሰላም ጥሪውን ተቀብለው ለገቡ ወጣቶች የተሐድሶ ሥልጠና እየተሠጠ ነው

By Shambel Mihret

December 31, 2023

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከማዕከላዊ ጎንደር ዞን እና ከጎንደር ከተማ አሥተዳደር የሰላም ጥሪውን ተቀብለው ለገቡ 850 ወጣቶች የተሃድሶ ሥልጠና እየተሠጠ መሆኑን የጎንደር ቀጣና ኮማንድ ፖስት አስታወቀ፡፡

ሠልጣኞቹ ከሥልጠናው ጎን ለጎን በጎንደር ከተማ የኢንቨስትመንት እና የልማት ቦታዎችን ጎብኝተዋል።

የጎንደር ቀጣና ኮማንድ ፖስት የሥልጠና ማዕከል አስተባባሪ አቶ አቤል መብት እንደገለጹት÷ ከዚህ ቀደም የሰላም ጥሪውን ተቀብለው ለገቡ ኃይሎች በሦስት ዙር ሥልጠና ተሰጥቷል።

ወጣቶቹ ከሥልጠናው በኋላ የሰላም አምባሳደር እንዲሆኑ እና ወደሥራ እንዲሰማሩ የተጀመሩ ተግባራት መኖራቸውንም ተናግረዋል።

የአማራ ክልል መንገድ ቢሮ ምክትል ኀላፊ ታደሰ ይርዳው በበኩላቸው÷ ሥልጠናው ተግባር ተኮር እንዲሆን እቅድ ተይዞ ወደ ሥራ መገባቱን ገልጸዋል።

ቢሮው የሥራ እድል ትስስር ለመፍጠር እንደሚሠራም መግለጻቸውን አሚኮ ዘግቧል፡፡

በጉብኝቱ የተገኙት የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኀላፊ በሪሁን መንግሥቱ÷ ባለፉት አምስት ወራት ክልሉ በሰላም እጦት ምክንያት በርካታ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ ገጥሞት ቆይቷል ብለዋል።

በዚህም የልማት ሥራዎች ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩን በመግለጽ፤ ለሰላም መስፈን ትልቁን ድርሻ የሚወስዱ ወጣቶች የልማት ሥራዎች ላይ እንዲሳተፉ ጠይቀዋል።

ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ እና የተቀዛቀዙ የልማት ሥራዎች እንዲፋጠኑ የመነጋገር እና የመደማመጥ ባሕልን ማሳደግ እንደሚያስፈልግም አንስተዋል።

ሠልጣኞቹ ቀዳማዊት ዝናሽ ታያቸው በጎንደር ከተማ ያስገነቡትን የዳቦ ፋብሪካ እና በከተማው ያሉ የዶሮ ርባታ ቦታዎችን ተጎብኝተዋል።