የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያ ብሪክስን በይፋ ተቀላቀለች

By Melaku Gedif

January 01, 2024

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያን ጨምሮ አምስት ሀገሮች ከዛሬ ጀምሮ ብሪክስ አባልነትን በይፋ ተቀላቅለዋል።

ከኢትዮጵያ በተጨማሪ የብሪክስ አባልነትን የተቀላቀሉት ሀገሮች ሳዑዲ አረቢያ፣ ግብጽ፣ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች እና ኢራን መሆናቸውን የሲጂቲኤን ዘገባ አመልክቷል።

ሀገራቱ በ2023 በደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ በተካሄደው 15ኛው የአባል ሀገራቱ ጉባዔ ብሪክስን እንዲቀላቀሉ ግብዣ እንደቀረበላቸው የሚታወስ ነው፡፡

በብራዚል፣ ሩሲያ፣ ሕንድ፣ ቻይናን እና ደቡብ አፍሪካን የተመሰረተው ብሪክስ አሁን ላይ የአባል ሀገራቱን ቁጥር ወደ 11 ከፍ ብሏል።

የብሪክስ አባል ሀገራት ከዓለማችን ህዝብ 40 በመቶ የሚገኝባቸው፣ 26 በመቶ የዓለምን የምርት ምጣኔ የሚሸፍኑ እና 50 በመቶ የሚጠጋ የዓለም ኢኮኖሚ እድገት ባለቤቶች ናቸው።

ጥምረቱ አዲስ አባል ሀገራቱን መጨመሩ በዓለም የዲፕሎማሲ፣ ንግድና ኢኮኖሚ ዘርፍ ያለውን ተጽእኖ እንደሚያሳድግለት ተንታኞች ይገልጻሉ።

የብሪክስ አባል ሀገራት በዓለም አቀፍ ንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ ፋይናንስ ስርዓትና አስተዳደር ላይ ያላቸው ትብብር እያደገ በመሄድ ላይ መሆኑም ተመላክቷል፡፡

በጆሃንስበርጉ ጉባኤ አርጀንቲና ያቀረበችው የአባልነት ጥያቄ ተቀባይነት ያገኘ ቢሆንም ከአንድ ወር በፊት የሀገሪቷ ፕሬዝዳንት ሆነው የተሾሙት ጃቪየር ሜሌ ከሳቸው በፊት የነበሩትን ፕሬዝዳንት አልቤርቶ ፈርናንዴዝ የአባልነት ጥያቄ በመሻራቸው ብሪክስን እንደማትቀላቀል ተገልጿል።