የሀገር ውስጥ ዜና

ሥምምነቱ የኢትዮጵያና ሶማሌ ላንድን ከጎረቤቶች ጋር በጋራ የመልማት ተምሳሌትነትን የሚያሳይ ነው- የአማራ ክልል መንግስት

By Mikias Ayele

January 01, 2024

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ እና በሶማሌ ላንድ መካከል የተፈረመው ስምምነት ከጎረቤቶች  ሀገራት ጋር በጋራ የመልማት ተምሳሌትነትን የሚያሳይ ነው ሲል የአማራ ክልል መንግስት ገለጸ፡፡

የክልሉ መንግስት ኢትዮጵያ የባሕር በር የምታገኝበትን የመግባቢያ ሥምምነት መፈረሟን አስመልክቶ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፏል፡፡

በመልዕክቱም ÷ዛሬ የተፈረመው የትብብርና የአጋርነት ስምምነት ባለ በርካታ ማዕቀፎች፣ ሰላምና ደህንነትን በጋራ መጠበቅ የሚያስችል መሆኑ ከፍ ያለ ትርጉም የሚሰጠው ነው ብሏል።

ከዚህ ባሻገርም የትውልዱን የዘመናት ጥያቄ የነበረውን የባሕር በር ጥያቄ  መመለስ የሚያስችልና የኢትዮጵያና ሶማሌ ላንድን ከጎረቤቶች ጋር በጋራ የመልማት ተምሳሌትነትን የሚያሳይ መሆኑን ገልጿል።

በመሆኑም የክልሉ መንግስትና ሕዝብ ለመላው ኢትዮጵያዊያንና ሶማሌ ላንድ ሕዝቦች እንዲሁም  ወዳጆች የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፏል፡፡