አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና የኦሮሚያ ባንክ በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሥምምነት ተፈራርመዋል፡፡
ሥምምነቱን የፈረሙት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) እና የኦሮሚያ ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተፈሪ መኮንን ናቸው፡፡
ሥምምነቱ የአዲስ አበባ ዩኒቨርቲ የራስገዝነት ትግበራ እና የሪፎርም ሥራ አንዱ አካል መሆኑ በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ወቅት ተገልጿል፡፡
ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) እንዳሉት÷ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባለፉት 73 ዓመታት ለሀገር ያበረከተውን አስተዋጽኦ በተሻለ አፈጻጸም እና ብቃት ለማስቀጠል እየተሠራ ነው፡፡
ዩኒቨርሲቲው ራስ ገዝ እንዲሆን መደረጉም ከተለያዩ ዘርፎች እና ኢንዱስትሪዎች ጋር በትብብር እንዲሠራ ያስችለዋል ብለዋል፡፡
ከኦሮሚያ ባንክ ጋር የተደረገው ሥምምነትም በፋይናንስ፣ በዕውቀት፣ በጥናት እና ምርምር፣ በተግባር ተሞክሮ ልውውጥ ተግባራት እና በመሰል ዘርፎች ተባብሮ ለመሥራት የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ለመምህራን የሚኖር ጥቅማ ጥቅምን ለማስጠበቅም ሥምምነቱ እንደሚያግዝ ጠቁመዋል፡፡
አቶ ተፈሪ መኮንን በበኩላቸው ባንኩ ለሀገር ልዩ አስተዋጽኦ እያበረከተ ከሚገኘው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር መሥራቱ ልዩ ትርጉም አለው ብለዋል፡፡
የኦሮሚያ ባንክ በአገልግሎት ልኅቀት እያደገ ያለ ባንክ መሆኑንም አንስተዋል። በለይኩን ዓለም