አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሰላም ግንባታና ብሔራዊ መግባባት ሂደትን ውጤታማ ማድረግ ያስችላል የተባለ ”ሀገር አቀፍ የሰላም ፎረም ጥምረት” ተመሰረተ።
ጥምረቱን ለመመስረት የተዘጋጀ መድረክ በአዳማ ከተማ የተካሄደ ሲሆን፥ በመድረኩ ላይ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሰላም ፎረም አመራሮች ተሳትፈዋል።
በሰላም ሚኒስቴር የሰላም ግንባታ ዴስክ ኃላፊ ወንድወሰን መኮንን እንደገለፁት፥ ፎረሙ በሰላም ግንባታና ብሔራዊ መግባባት ላይ ትልቅ ሚና ይጫወታል።
ከዚህ ቀደም ተመስርቶ የሚገኘው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሰላም ፎረም የሀገር አቀፍ የሰላም ፎረም ጥምረት አባል እንደሚሆንም ነው የተናገሩት።
በዚህም በሀገር አቀፍ ደረጃ ጠንካራ የሰላም ፎረም አደረጃጀትና ወጥነት ያለው አሰራር በመፍጠር የሰላም ግንባታና ብሔራዊ መግባባቱን ውጤታማ ለማድረግ መታሰቡን አስረድተዋል።
የትምህርት ሚኒስቴርና የሰላም ሚኒስቴር የሰላም ፎረሙን የጋራ ዕቅድና የድርጊት መርሐ ግብር በመንደፍ በትብብር እንደሚመሩት መጥቀሳቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።
በመድረኩ ላይ የተሳተፉት የትምህርት ሚኒስቴር ተወካይ ኤዶሳ ተርፋሳ (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ በትምህርት ተቋማት የሰላም ግንባታው እንቅስቃሴ ውጤታማ እየሆነ መምጣቱን ገልጸዋል።
በዩኒቨርሲቲዎች ያሉ የሰላም ፎረምና የተማሪዎች ህብረት በትብብር በመስራታቸው በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አካባቢ ያለው ሰላም እየተሻሻለ እንዲመጣ ማድረጉን አክለዋል።
በተለይም የተማሪዎች ህብረትና የዩኒቨርሲቲዎች የሰላም ፎረም የጋራ እቅድ አዘጋጅተው በቅንጅት እንዲሰሩ በመደረጉ የተሻለ ውጤት እየተገኘ መሆኑንም ነው ኤዶሳ (ዶ/ር) የተናገሩት።
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- FBC(Fana Broadcasting Corporate S.C.) ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/ ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!