አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በግብርና ምርት አቀነባባሪዎች አማካኝነት ቋሚ የገበያ ትስስር የተፈጠረላቸው አርሶ አደሮች ህይወት እየተሻሻለ መሆኑን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ገለጸ፡፡
የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ አክሊሉ ታደሰ ከሌሎች የሥራ ሀላፊዎች ጋር በመሆን በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ የቢራ ገብስ ብቅል ማቀነባበር ስራ ላይ ለተሰማራው ሱፍሌ ለተሰኘው የፈረንሳይ ኩባንያ የቢራ ገብስ የሚያቀርቡ አርሶ አደሮችን ስራ ጎብኝተዋል፡፡
በጉብኝታቸውም በምዕራብ አርሲ ዞን በሚገኙት በሻሸመኔ ወረዳ ሁርሳ የሚገኙ አርሶ አደሮችን ተመልክተዋል፡፡
ዋና ስራ አስፈጻሚው በወቅቱ÷ አርሶ አደሮቹ በተፈጠረላቸው የገበያ ትስስር ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ከማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው በተጨማሪ ኮርፖሬሽኑ በግብርና ምርቶች ማቀነባበር ዘርፍ የተሰማሩ ኩባንያዎች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
አርሶ አደሮቹ ከ60 ሺህ ቶን በላይ ለቢራ ምርት የሚውል ገብስ ለሱፍሌ ኩባንያ ግብዓት የሚያቀርቡ መሆናቸውን የኮርፖሬሽ መረጃ ያመላክታል፡፡
በዚህም ኢትዮጵያ የብቅል ምርትን ከውጪ ለማስገባት የምታወጣውን የውጪ ምንዛሪ በማስቀረት በሀገር ውስጥ ምርት እንዲሸፈን በማድረግ በኩል ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረከቱ ናቸው ተብሏል።
በቀጣይ በባህርዳር በአኩሪ አተር እንዲሁም በድሬዳዋ ከግመል ወተት የግመል የዱቄት ወተት ለሚያመርቱ ግዙፍ ኩባንያዎች ግብዓት የሚያቀርቡ አርሶና አርብቶ አደሮች ወደ ስራ እንደሚገቡ ተመላክቷል፡፡
ኮርፖሬሽኑ በቦሌ ለሚ፣ በደብረብርሀን እና በጅማ በሚያስተዳድራቸው ፓርኮች እንዲሁም በቅርቡ በድሬዳዋ ነፃ ንግድ ቀጠና በግብርና ምርት ማቀነባበር ዘርፍ ለተሰማሩ ኩባንያዎች ግብዓት የሚያቀርቡ አርብቶ አደሮችን ጨምሮ ከ110 ሺህ በላይ የሚሆኑ አርሶ አደሮች ዘላቂ የገበያ ትስስር ተፈጥሮላቸዋል ነው የተባለው።