የሀገር ውስጥ ዜና

በኦሮሚያ ክልል ከግማሽ ሚሊየን በላይ ሰዎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የውኃ ፕሮጀክቶች ለአገልግሎት በቅተዋል

By ዮሐንስ ደርበው

January 03, 2024

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል በተጠናቀቀው ግማሽ ዓመት ከ500 ሺህ በላይ ወገኖችን መድረስ የቻሉ 2 ሺህ 618 የውኃ ፕሮጀክቶች ለአገልግሎት ክፍት መደረጋቸውን የክልሉ ውኃና ኢነርጂ ቢሮ አስታወቀ፡፡

የቢሮው ምክትል ኃላፊ መሐመድ ኑራ (ኢ/ር) ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንዳሉት÷ በግማሽ ዓመቱ ለአገልግሎት ክፍት ለተደረጉት እና አሁንም ግንባታቸው ወደ መጠናቀቁ ለተቃረቡ የውኃ ፕሮጀክቶች 4 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ወጪ ተደርጓል፡፡

ወጪውም÷ በክልሉ መንግሥት፣ መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች፣ በሕብረተሰብ ተሳትፎ እና በፕሮግራሞች (ከተለያዩ የልማት አጋሮች በተገኘ ድጋፍ) መሸፈኑን አብራርተዋል፡፡

በአጠቃላይ በ2016 በጀት ዓመት 11 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ተመድቦ ከ10 ሺህ በላይ የውኃ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከ11 ነጥብ 3 ቢሊየኑ ብር 7 ነጥብ 6 ቢሊየኑ በክልሉ መንግስት እንደሚሸፈንም ነው ያረጋገጡት፡፡

ባለፉት ሥድስት ወራት ያልተጠናቀቁትን ጨምሮ ሌሎች ፕሮጀክቶችን በበጀት ዓመቱ ለማጠናቀቅ እየሠሩ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

በዮሐንስ ደርበው