አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት ለገና በዓል ጤናማነቱ የተረጋገጠ የዕርድ አገልግሎት ለመሥጠት ዝግጅት ማድረጉን አስታወቀ።
የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰይድ እንድሪስ÷ የበዓል የሥጋ አቅርቦትን በተመለከተ ከአዲስ አበባ አርሶ አደርና የከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን እንዲሁም ከመዲናዋ የልኳንዳ ነጋዴዎች ማሕበር ጋር በመሆን መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም÷ ለበዓሉ ዕርድ 3 ሺህ በሬዎች፣ 5 ሺህ በጎች እና ፍየሎች መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
የሥጋ አቅርቦቱን ተደራሽ ለማድረግም በቂ ተሽከርካዎችና ሠራተኞች መኖራቸውን በመግለጽ÷ ድርጅቱ ደኅንነቱ የተጠበቀና ጤናማነቱ የተረጋገጠ የዕርድ አገልግሎት ለመሥጠትም ዝግጅት ማድረጉን መግለጻቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡
የአዲስ አበባ አርሶ አደርና የከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን የሥጋ ምርመራ አስተባባሪ ከበባ ኤርቤቱ (ዶ/ር)÷ የዕርድ እንሰሳትን ለማሕበረሰቡ ለማቅረብ በእንስሳሰቱ ላይ አሥፈላጊው የጤና ምርመራ መደረጉን ተናግረዋል።