አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለገና (ልደት) እና ጥምቀት በዓላት አስፈላጊ የሆኑ ምርቶች አቅርቦት እጥረት እንዳያጋጥም ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሠራ መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
በዓላቱን ታሳቢ ያደረገ መነሻ ዕቅድ ተዘጋጅቶ÷ ለዋጋ ንረት ማረጋጋት እና ሕገ-ወጥ ንግድ መካላከል ግብረ-ኃይል፣ ለግብርና ሚኒስቴር፣ ለኅብረት ሥራ ማኅበራት ኮሚሽን፣ ለንግድ ቢሮዎች፣ ለመንግሥት የልማት ድርጅቶች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት መላኩ እና ምክክር መደረጉም ተገልጿል፡፡
በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የሀገር ውስጥ ንግድና ሸማቾች ጥበቃ መሪ ሥራ አስፈጻሚ መስከረም ባሕሩ እንዳሉት÷ ያልተነሳ (ያልተሰራጨ) 9 ነጥብ 8 ሚሊየን ሊትር ዘይት ክልሎች ወስደው ለሕብረተሰቡ እንዲያሰራጩ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡
እንዲሁም በተጠናቀቀው ግማሽ ዓመት በፍራንኮ ቫሉታ አማካኝነት 8 ነጥብ 6 ሚሊየን ሊትር እንዲሁም 3 ነጥብ 2 ሚሊየን ኩንታል ስኳር ወደ ሀገር ውስጥ መግባቱንም ጠቁመዋል፡፡
አሁን ላይ በክምችት ያለውን የስኳር ምርት መጠን ግምት ውስጥ በማስገባትም ለከተማ አስተዳደሮች እና ክልሎች እንደሚሠራጭ ጠቅሰዋል፡፡
ዱቄትም ያለምንም ሥጋት እየቀረበ መሆኑንም በመስክ አረጋግጠናል ነው ያሉት፡፡
አምራችና ሸማችን በቀጥታ ከማገናኘት አንጻር 856 የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ እንደ አካባቢዎቹ ሁኔታም ተጨማሪ የገበያ ትስስር መፍጠሪያ አማራጮች እንደሚኖሩ አመላክተዋል፡፡
ከሕገ-ወጥ ግብይት ጋር በተያያዘ የክትትልና ቁጥጥር ሥራው እንደሚጠናከር ገልጸዋል፡፡
በዮሐንስ ደርበው
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- FBC(Fana Broadcasting Corporate S.C.) ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/ ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!