አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ እና ሶማሊ ላንድ መካከል የተፈረመውን የመግባቢያ ሠነድ በተመለከተ መቀመጫቸውን አዲስ አበበ ላደረጉ የዲፕሎማቲክ ማኀበረሰብ አባላት ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ሚኒስትር አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በማብራሪያው ላይ እንደገለጹት÷ አዲስ የተፈረመው የመግባቢያ ሠነድ ለኢትዮጵያ የባሕር በር እና የወደብ አማራጮችን ያሰፋል፡፡
ሠነዱ በቀጣናው ሰላም እና ደኅንነት ከማስጠበቅ አንጻር ትልቅ ሚና አለው ማለታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡
የፍትሕ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ የመግባቢያ ሠነዱ ለኢትዮጵያ የባሕር በር እና ወደብ ከማስገኘቱ ባሻገር በተፈራረሙት ሀገራት መካከል የንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ ቴክኖሎጂ፣ ግብርና እና ቱሪዝም ትብብርና አጋርነትን ስለማካተቱ አብራርተዋል፡፡
የጠቅላይ ሚንስትሩ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አማካሪ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ኢትዮጵያ በሰላማዊ መንገድ የባሕር በር እና የወደብ ባለቤት መሆን እንደሚቻል አሳይታለች ብለዋል።