አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችው የመግባቢያ ሥምምነት የሁለቱን ሀገራት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እንደሚያረጋግጥና ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትብብር እንደሚፈጥር ተገለጸ፡፡
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሺዴ፥ ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችውን በርበራ ወደብን ለረጅም ጊዜ መጠቀም የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ በተመለከተ ለተቋማቸው አመራሮችና ሰራተኞች ገለጻ አድርገዋል፡፡
ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት ሥምምነቱ ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ በጋራ እንዲለሙ ከማድረጉም በላይ በቀጣናው ሀገራት መካከል ኢኮኖሚያዊ ትብብር በመፍጠር የላቀ አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቁመዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገሮች ጋር የጀመረችው ኢኮኖያዊ ትብብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በመግለጽ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እያደገ የሚሄድ በመሆኑ ይህን ኢኮኖሚ የሚያስተናግድ የወደብና የሎጂስቲክ ግንኙነት ከጅቡቲ፣ከኬንያና ከሌሎችም ሀገራት ጋር ግንኙነቱ እንደሚቀጥልና ኢኮኖሚያዊ ትስስሩ እየዳበረ እንደሚሄድ አመላክተዋል፡፡
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ በሕጋዊ መንገድ የወደብ ባለቤትና ተጠቃሚ መሆናችን ኢኮኖሚያዊ ብቻ ሳይሆን ሁለንተናዊ ጥቅም ያለው በመሆኑ ታላቅ ሀገራዊ ድል ነው ብለዋል፡፡
የሚኒስቴሩ ሰራተኞችም በዚህ ለረጅም ጊዜ በቁጭትና በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው ሃገራዊ አጀንዳ እውን መሆን ደስታቸውን እንደገለጹ የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡