የሀገር ውስጥ ዜና

ኮሚሽኑ በአሜሪካና ካናዳ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር የፊታችን ጥር 5 ቀን ይወያያል

By Melaku Gedif

January 03, 2024

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአሜሪካ እና ካናዳ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር የፊታችን ጥር 5 ቀን 2016 ዓ.ም እንደሚወያይ አስታውቋል፡፡

ኮሚሽኑ በመላው ዓለም ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር የበይነ-መረብ ስብሰባ በማድረግ ላይ መሆኑ ይታወቃል፡፡

በዚህም መሰረት ኮሚሽኑ በአሜሪካ እና ካናዳ ከሚኖሩ ወገኖች ጋር እሑድ ጥር 05 ቀን 2016 ዓ.ም ወይም በፈረንጆቹ የፊታችን ጥር 14 ቀን ውይይት እንደሚያካሂድ ገልጿል፡፡

ስለሆነም በሀገራቱ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ከሰዓት በኋላ 11 ሰዓት (5PM at GMT+3) ማለትም 9:00 AM ጀምሮ በሚካሄደው የበይነ-መረብ ስብሰባ እንዲካፈሉ ጥሪ ቀርቧል፡፡

በስብሰባው ላይ ለመሳተፍ ከዚህ በፊት የተመዘገቡ መኖራቸውን የጠቀሰው ኮሚሽኑ÷ ያልተመዘገቡ ወገኖች https://forms.gle/VG9HtwD5Cnw1cMe4A ሊንኩን በመጫን መመዝገብ እንደሚችሉ አስታውቋል፡፡

ኮሚሽኑ በስብሰባው ላይ ለመሳተፍ ለተመዘገቡ ወገኖች በኢሜል አድራሻቸው የመሰብሰቢያ ሊንኩን እንደሚልክ ጠቁሟል፡፡