አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በጅማ ከተማ 10 ሺህ ካሬ ሜትር ይዞታን ላልተገባ ጥቅም በማዋል መንግስትን ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ አሳጥተዋል የተባሉ ተከሳሾች በ15 አመት ጽኑ እስራት እና በገንዘብ እንዲቀጡ የጅማ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ወንጀል ችሎት ወሰነ።
የቅጣት ውሳኔው የተላለፈባቸው ተከሳሾች የጅማ ከተማ ማዘጋጃ ቤት የቀድሞ ፕላንና መሬት አስተዳደር ኃላፊ ሼራብ አባሜጫ አባጎጃም እና የጅማ ከተማ የቀድሞ ጤና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አወል አባሜጫ አባቡሉ ናቸው።
የጅማ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ተከሳሾቹን በቁጥጥር ስር አውሎ የተለያዩ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን በማሰባሰብ የምርመራ መዝገቡን ለኦሮሚያ ክልል ጅማ ዞን ዐቃቤ ሕግ አስረክቧል።
ዐቃቤ ሕግም ተከሳሾቹን በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢፌዲሪ የወንጀል ህግ አንቀጽ 32 ንዑስ ቁጥር 1 ሀ እና ለ አንቀጽ 407 ንዑስ ቁጥር 3 ስር የተመላከተውን ድንጋጌ ተላልፈዋል በማለት በመጋቢት 26 ቀን 2015 ዓ.ም ተደራራቢ ክስ አቅርቦባቸዋል።
በክሱ ላይ እንደተመላከተው ተከሳሾቹ በቁጥጥር ስር ያልዋለው በክስ መዝገቡ በ3ኛ ተራ ቁጥር ከተጠቀሰው የጅማ ከተማ የመሃንዲስ መሪ ከነበረው ሰዓዲ አቢዩ ነገኦ ከተባ ተከሳሽ ጋር በጥቅም በመመሳጠር 2ኛ ተከሳሽ በወላጅ እናቱ ስም እና ፊርማቸውን አስመስሎ በመጠቀም 10 ሺህ ካሬ ሜትር ይዞታ እንዲሰጣቸው ጥያቄ ያቀረበ በማስመሰል ማመልከቻ ማስገባቱ ተጠቅሷል።
በማመልከቻው መነሻነት 1ኛ ተከሳሽና 3ኛ ተከሳሽ በጋራ በመሆን አንድ ካሬ ሜትር በ1 ብር ከ50 ሳንቲም በሊዝ የተሰጠ አስመስለው ለ2ኛ ተከሳሽ በጊንጆው ጉድሉ ቀበሌ 10 ሺህ ካሬ ሜትር ይዞታ እንዲወስድ ማድረጋቸው በክሱ ተገልጿል።
በተጨማሪም ለክሊኒክ ግንባታ በሚል በ3ኛ ተከሳሽ ፕላንና ካርታ አዘጋጅነት በ1ኛ ተከሳሽ አጽዳቂነት መስጠታቸው ተዘርዝሯል።
ባጠቃላይ ይዞታው በሊዝ ቢሸጥ ኖሮ ሊገኝ የሚችለውን ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ማሳጣታቸው በክሱ ተጠቅሷል።
በዚህ መልኩ ፍርድ ቤት ቀርበው የቀረበባቸውን ክስ የተከታተሉት 1ኛና 2ኛ ተከሳሾች ወንጀሉን አለመፈጸማቸውን ጠቅሰው በሰጡት የዕምነት ክህደት ቃል መነሻ ፍርድ ቤቱ በዐቃቤ ሕግ የቀረቡ የተለያዩ የምስክር ቃልና የሰነድ ማስረጃዎችን ተመልክቷል።
የቀረበባቸውን ማስረጃ እንዲከላከሉ ብይን የተሰጣቸው ተከሳሾቹ የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን በተገቢው መስተባበል ባለመቻላቸው በተከሰሱበት ድንጋጌ የጥፋተኝነት ፍርድ ተላልፎባቸዋል።
ፍርድ ቤቱ በዐቃቤ ሕግ በኩል ተከሳሾቹ ወንጀሉን በጥቅም በመመሳጠር የፈጸሙት መሆኑ ተጠቅሶ የቀረበውን የቅጣት ማክበጃ እና የተከሳሾቹ የቤተሰብ አስተዳዳሪና የቀደመ የወንጀል ሪከርድ እንደሌለባቸው ያቀረቡትን የቅጣት ማቅለያ ይዟል።
በዚህም ፍርድ ቤቱ ዛሬ በዋለው ችሎት ተከሳሾቹ እያንዳንዳቸውን በ15 አመት ጽኑ እስራትና በ20 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ መወሰኑን የጅማ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የኮሙኒኬሽንና ሚዲያ ዲቪዢን ኃላፊ ም/ኮማንደር ገዛኸኝ አጉቾ ገልጸዋል።
በታሪክ አዱኛ