አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት አምስት ወራት ከ144 ሺህ 825 በላይ ዜጎች ለሥራ ወደ ውጪ መሰማራታቸውን የሥራ እና ክሕሎት ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
የውጭ ሀገር የሰራተኛ ስምሪት የዜጎችን መብት፣ ደህንነትና ጥቅም በማስጠበቅ የኢትዮጵያን ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ መልኩ የተጀመሩ ሥራዎች የደረሱበት ደረጃ ተገምግመዋል፡፡
በመድረኩ የሥራ እና ክሕሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል፣ አምባሳደር ግርማ ብሩ፣ ባለድርሻ አካላትና ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
ወ/ሮ ሙፈሪሃት÷ በዘርፉ የዜጎችን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ባለፉት አምስት ወራት ከ144 ሺህ 825 በላይ ዜጎችን ለሥራ ወደ ውጪ ማሰማራት መቻሉን ተናግረዋል፡፡
በዚህም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣ አፈጻጸም መመዝገቡን ጠቁመው÷ ለበርካታ ዜጎች ጥራት ያለው የሥራ ዕድል መፍጠር የሚያስችል አቅም መገንባቱንም በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው አስፍረዋል፡፡
በዚህም የተጀመሩ ሥራዎች በጥሩ ደረጃ ላይ መሆናቸውን እና በባለድርሻ አካላት መካከል የተጀመረውን ጠንካራ የቅንጅት ሥራ አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ አቅጣጫ መቀመጡን ጠቁመዋል፡፡