አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያና ሶማሊላንድ የተፈራረሙት የመግባቢያ ስምምነት ለአህጉራዊ የኢኮኖሚ ልማት ጥሩ ማሳያ መሆኑን አሜሪካዊው የአፍሪካ ፖለቲካና ኢኮኖሚ ጉዳዮች ተንታኝ ላውረንስ ፍሪማን ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እና የሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲ ኢትዮጵያ የባህር በር ማግኘት የሚያስችላትን የመግባቢያ መፈራረማቸው ይታወቃል፡፡
አሜሪካዊው የአፍሪካ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ጉዳዮች ተንታኝ ላውረንስ ፍሪማን እንዳሉት ፥ ስምምነቱ ለአህጉራዊ የኢኮኖሚ ልማትና እድገት በጥሩ ምሳሌነት የሚጠቀስ ነው።
ለኢትዮጵያና ሶማሊላንድ የኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ፣ የፖለቲካና ወታደራዊ ትብብርም የላቀ ፋይዳ ያለው መሆኑንም ነው ያብራሩት።
ከአፍሪካ ከፍተኛውን ቁጥር ከያዙት ሀገራት መካከል የምትጠቀሰው ኢትዮጵያ ለረጅም ዓመታት ያለ ባህር በር መቆየቷ ጉዳቱ ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ስምምነቱም የጋራ ተጠቃሚነትና ሰፊ የመልማት እድል የሚፈጥርላትና ብሎም አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን ነው የተናገሩት።
በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር የሚያቀጣጥሉ የፖለቲካ ሃይሎች መኖራቸውን የጠቀሱት የፖለቲካ ተመራማሪው ፥ እንዲህ ዓይነት እኩይ ተግባር ለቀጣናው የማይበጅ ነው ሲሉ አብራርተዋል።
በአፍሪካ እምቅ የተፈጥሮ ሃብቶችን በጋራና በትብብር በማልማት መጠቀም ለአህጉራዊ እድገት ወሳኝ መሆኑንም ነው የገለጹት።
የኢትዮጵያና ሱማሊላንድ የባህር በር ስምምነት በአህጉራዊና ዓለም አቀፍ የንግድና ኢንቨስትመንት ትስስሮች ኢትዮጵያን ይበልጥ ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ግዙፍ ምጣኔ ሃብትና በርካታ የህዝብ ቁጥር ያላት ሀገር በመሆኗ የባህር በሩን በመጠቀም ትልቅ የባህር ሃይል ለመገንባት ያስችላታልም ነው ያሉት።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል መሆኗም ለምጣኔ ሃብት እድገቷ ተጨማሪ እድል መሆኑን ጠቅሰው ፥ አዲስ ትብብርን የሚፈጥር ስለመሆኑም አንስተዋል።