አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ዓባይ ቴሌቪዝን የኅብረተሰቡን መልካም ባህል እና ዕሴት የሚጥሱ ሐሳብ ያለበት ፕሮግራም አስተላልፏል በሚል የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ መስጠቱን አስታወቀ፡፡
ባለሥልጣኑ ለቴሌቪዥን ጣቢያው በጻፈው የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ደብዳቤ፥ ዓባይ ቴሌቪዥን እሑድ ታኅሣሥ 28 ቀን 2016 ዓ.ም ‘ዋሸሁ እንዴ?’ የተሰኘ ፕሮግራሙ ላይ የሴቶችን ስብዕና፣ መብት እና ክብር የሚያጎድፉ እንዲሁም የኅብረተሰቡን መልካም ባህል እና ዕሴት የሚጥሱ መሆኑን ጠቁሟል፡፡
በተለይም በሴት ልጆች ላይ የሚፈጸም ወንጀልን የሚያበረታቱ እና ታዳጊዎችን ላልተገባ ድርጊት የሚዳርጉ ሐሳብ እና አስተያየቶች በፕሮግራሙ ላይ መተላለፋቸውን ባለሥልጣኑ ያደረገው የሚዲያ ይዘት ክትትል ግኝት እንደሚያመለክትም ነው በመግለጫው ያነሳው፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ከኅብረተሰቡም ጥቆማዎች መቅረቡን ገልጿል።
ባለሥልጣኑ በዕለቱ የተሠራጨው ፕሮግራም የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ 1238/2013 አንቀጽ 68/2 ለ/ሐ/መ/ እና ሠ ላይ የተቀመጡ ድንጋጌዎችን የጣሰ ሆኖ መገኘቱንም ነው የጠቆመው፡፡
ዓባይ ቴሌቪዥን በተደጋጋሚ የኅብረተሰቡን መልካም ዕሴት፣ ሰላም እና ደኅንነት የሚያናጉ ፕሮግራሞች እና ዘገባዎችን በጣቢያው ሲያሠራጭ ከባለሥልጣኑ በኩል በተለያዩ መንገዶች ግብረ-መልሶችን ተሰጥቶታል።
እንዲሁም ከጣቢያው ኃላፊዎች ጋር ውይይቶችን በማካሄድ ጭምር መሻሻሎች እንዲደረጉ ጥረት ቢደረግም ጣቢያው ይህን መሰል ድርጊቶችን ለማረም አልቻለም ሲልም ባለስልጣኑ ገልጿል።
በመሆኑም ጣቢያው በቀጣይ መሰል ሕግን የሚጥሱ፣ ኃላፊነት የጎደላቸው፣ የሰውን ልጅ ስብዕና እና ደኅንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ ፕሮግራሞችን ከማሠራጨት እንዲቆጠብ ይህ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጠውም በመግለጫው ተነስቷል።