የሀገር ውስጥ ዜና

በመዲናዋ ከ10 ሺህ በላይ የሺሻ መጠቀሚያ እቃዎችና 70 ኪሎ ግራም አደንዛዥ ዕፅ መወገዱ ተገለጸ

By Shambel Mihret

January 11, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥር 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በቦሌ እና በቂርቆስ ክፍለ ከተሞች በተለያየ ጊዜ የተሰበሰቡ ከ10 ሺህ በላይ የሺሻ መጠቀሚያ እቃዎች እና 70 ኪሎ ግራም አደንዛዥ ዕፅ መወገዱን የአዲስ አበባ ፖሊስ ገለጸ፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ ለወንጀል መስፋፋት መንስኤ በሆኑ ጉዳዩች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝም ገልጿል፡፡

በታኅሣስ ወር ብቻ ሺሻ በሚያስጨሱ ሕገወጦች ላይ በ11ዱም ክፍለ ከተሞች በተወሰደ እርምጃ በርካታ የሺሻ ማስጨሻ እቃ መያዙ ተጠቅሷል፡፡

የቦሌና የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያዎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላትና የሀገር ሽማግሌዎች በተገኙበት ዛሬ 10 ሺህ 550 የሺሻ መጠቀሚያ እቃዎችና 74 ኪሎ ግራም ካናቢስ የተባለ አደንዛዥ ዕፅ ተወግዷልም ነው የተባለው፡፡

የቦሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ረ/ኮሚሽነር አድማሱ ኢፋ በዚሁ ወቅት ÷ ከህብረተሠቡ የሚመጡ ጥቆማዎችን መነሻ በማድረግ 5 ሺህ 580 የሺሻ እቃዎችና 74 ኪሎ ግራም አደንዛዥ እፅ በመያዝ እንዲወገድ መደረጉን ተናግረዋል፡፡

የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ረ/ኮሚሽነር ደመና ተስፋዬ በበኩላቸው ÷ 4 ሺህ 970 የሺሻ እቃዎች ን መያዝ እንደተቻለ መግለጻቸውን ነው የፖሊስ መረጃ የሚያመላክተው፡፡

ፖሊስ የከተማዋን ሠላምና ደህነት ለማረጋገጥ ዘርፈ ብዙ ስራዎች እየሠራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በአዲስ አበባ ፖሊስ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ም/ኮማንደር ማርቆስ ታደሠ ናቸው፡፡