የሀገር ውስጥ ዜና

ብቃት ባለው አመራርና በሕዝብ ተሳትፎ የተሻሉ ከተሞች የሚገኙበት ክልል መፍጠር ይገባል – አቶ ጥላሁን ከበደ

By Melaku Gedif

January 12, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥር 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ብቃት ባለው አመራር፣ በሕዝቦች ባለቤትነትና ተሳትፎ ከተሞችን የብልፅግና ተምሳሌት ማድረግ ያስፈልጋል ሲሉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ገለጹ፡፡

“ባለብዙ ፀጋ ከተሞቻችን በነዋሪዎች ተሳትፎና ባለቤትነት ወደ ብልፅግና ተምሳሌትነት” በሚል መሪ ሃሳብ ከተማ አቀፍ የንቅናቄ መድረክ በአርባ ምንጭ ከተማ እየተካሄደ ነው።

አቶ ጥላሁን በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት÷ በክልሉ ከተሞች ሳይሆኑ የከተማነት ስያሜን የያዙ በርካታ መዋቅሮች እንደሚገኙ አስገንዝበዋል፡፡

የከተሞች ምጣኔ እሳቤው የከተማ ገጠር መስፋፋት ትስስርን ጤናማ ማድረግ እንደሆነ የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳድሩ÷ በርካታ ፖሊሲና ፕሮግራሞች ቢቀረፁም አብዛኞቹ መዋቅሮች ከደረጃ በታች እንደሆኑ ተናግረዋል።

ብቃት ባለው አመራር፣ በሕዝቦች ባለቤትነትና ተሳትፎ ከተሞችን የብልፅግና ተምሳሌት በማድረግ የተሻሉ ከተሞች የሚገኙበት ክልል መፍጠር እንደሚገባ አሳስበዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የከተማና መሠረተ-ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ዘውዴ በበኩላቸው÷ የክልሉን የከተሜነት ምጣኔ በተያዘው ዓመት አሁን ካለበት 22 በመቶ ወደ 25 በመቶ ለማሳደግ እንደሚሰራ ተቁመዋል፡፡

የከተሞች ዕድገት በዘፈቀደ እንዳይሆን ጥናት ተካሂዶ ወደ ሥራ እንደተገባ መናገራቸውንም የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡