የሀገር ውስጥ ዜና

የወንጪ ዳንዲ ነዋሪዎችን ሕይወት ያቀለለው ተንጠልጣይ ድልድይ

By Feven Bishaw

January 12, 2024

 

አዲስ አበባ፣ ጥር 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የወንጪ ዳንዲ ኢኮ ቱሪዝም መንደር ፕሮጀክት በግንባታ ሒደት ለበርካታ ዜጎች ከፈጠረው የሥራ ዕድል በተጨማሪ በመሰረተ ልማት ዕድሎች እና ሌሎች ዘርፎች ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ገለፁ።

የወንጪ ዳንዲ ልማት ወደ አካባቢው ካመጣቸው በርካታ ግዙፍ ፕሮጀክቶች መካከል 72 ሜትር የሚረዝመው ተንጠልጣይ ድልድይ ተጠቃሽ ነው።

ይህ ድልድይ ከመገንባቱ አስቀድሞ በውሃ ሙላትና ከመልካ ምድሩ አመቺ አለመሆን ጋር ተያይዞ መገናኘት አንችልም ነበር የሚሉት የአካባቢው ነዋሪዎች÷ ዛሬ ላይ ይህ እውነት ተቀይሯል ብለዋል።

የተንጠልጣይ ድልድዩ ግንባታ ሒደት ለአካባቢው ወጣቶች የሥራ ዕድልን ብቻ ሳይሆን የእውቀት እና የቴክኖሎጂ ሽግግር መፍጠሩም ተመላክቷል፡፡

በተንጠልጣይ ድልድይ ግንባታ ላይ የተሳተፉ ባለሙያዎች፥ አካባቢው ተራራማ መሆኑን ተከትሎ የግንባታ ግብዓቶችን እና ማሽነሪዎችን በቀላሉ ወደ ቦታው ለማጓጓዝ አስቸጋሪ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

የወንጪ ዳንዲ ኢኮ ቱሪዝም መንደርን በማልማት ሒደት 12 ሺህ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩ ነው የተገለጸው፡፡

የአካባቢው ማሕበረሰብም ቀድሞ ሳይጠቀምበት ከቆየው የተፈጥሮ ሃብት አሁን የላቀ የተጠቃሚነት ዕድል ማግኘቱ ተጠቁሟል።

በመራኦል ከድር