የሀገር ውስጥ ዜና

የመቀለ ከተማ አስተዳደር በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች የ50 ሚሊየን ብር ድጋፍ አደረገ

By Shambel Mihret

January 13, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥር 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በትግራይ ክልል የመቀለ ከተማ አስተዳደር በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች የሚሆን የ50 ሚሊየን ብር ድጋፍ አስረከበ፡፡

በድጋፍ ርክክብ ስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታቸው ረዳ÷ ያጋጠመውን ችግር ለመቋቋም ለተደረገው ድጋፍ አመስግነዋል፡፡

በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ያጋጠመው የድርቅ አደጋ ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ሌሎች አካላትም የመቀለ ከተማ አስተዳደርን አርዓያነት ሊከተሉ ይገባል ብለዋል፡፡

የመቀለ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ይትባረክ አመሓ በበኩላቸው÷ በድርቁ ምክንያት የተጎዱ ወገኖችን ለመደገፍ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም የአይደር ሪፈራል ሆስፒታል እና የመቀለ አጠቃላይ ሆስፒታል ያጋጠማቸውን የመድሐኒት እጥረት ለመፍታት የሚያግዝ ለእያንዳንዳቸው የ10 ሚሊየን ብር ድጋፍ መደረጉን የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡