የሀገር ውስጥ ዜና

የብልፅግና ፓርቲ የ6 ወር አፈፃፀም ግምገማ መድረክ ተጀመረ

By Shambel Mihret

January 16, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥር 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለሦስት ቀናት የሚቆየው የብልፅግና ፓርቲ የሥድስት ወር አፈፃፀም ግምገማ መድረክ በዛሬው ዕለት ተጀምሯል።

በመርሐ ግብሩ የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህን ጨምሮ የክልል ቅርንጫፍ ፅ/ቤት ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

በመድረኩ አቶ አደም ፋራህ እንደገለጹት ÷ በአመለካከትና በተግባር የተዋሃደ አመራርን በመፍጠር ቅቡልነት ያለው የሀገረ መንግስት ስርዓት ለመገንባት እንዲሁም የሕዝቡን ተሳትፎ፣ ተጠቃሚነትና ብሎም እርካታን ማረጋገጥ ዋና ዓላማው አድርጎ ፓርቲው በመንቀሳቀስ ላይ ነው።

በመድረኩ ባለፉት ሥድስት ወራት እንደ ፓርቲ ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ የተሄደበት ርቀት በጥልቅ እንደሚገመገም መግለጻቸውን ከፓርቲው የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

በተለይም በምርጫ ማግስት ፓርቲው ለህዝብ ቃል የገባቸውን የተፈፃሚነታቸው ደረጃ በምን ዓይነት እርከን ላይ እንደሚገኝ፣ በአምስቱ ሀገራዊ የልማት የትኩረት መስኮች የተገኙ ውጤቶች፣ የብሔራዊነት ትርክትን እንደ ሀገር ለመገንባት የሄደባቸው ርቀቶች በልዩ ትኩረት ምልከታ እንደሚደረግባቸው ተገልጿል፡፡

የአፈፃፀሙ መገምገም ፓርቲው ያለበትን ደረጃ ለመለየትና በቀጣይ የተግባራትን ስኬታማነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ እንዲሁም ውጤታማ የክትትልና ድጋፍ ሥርአት ለመዘርጋት የሚያስችል አቅም ለመፍጠር እንደሚያግዝም ነው የተጠቆመው፡፡

በግምገማ መድረኩ ላይ በዘርፎች የተከናወኑ የሥድስት ወራት ሪፖርት፣ በተለያዩ ክልሎች ውጤት የተገኘባቸው የፓርቲ ስራዎችና ተሞክሮዎች በሪፖርት መልክ እንደሚቀርቡ ይጠበቃል፡፡