አዲስ አበባ፣ ጥር 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሶማሌ ክልል ስራ አስፈፃሚ ምክር ቤት የ2016 በጀት አመት 9ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን አሳልፏል።
በዛሬው እለት በተካሄደው የስራ አስፈፃሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሙስጠፌ መሐመድ ተገኝተዋል፡፡
ስራ አስፈጻሚ ምክር ቤቱ በኢትዮጵያና በክልሉ ወቅታዊ ሁኔታ ዙሪያ መወያየቱን የክልሉ መገናኛ ብዙሀን ዘግቧል፡፡
በዚህም በክልሉ የሸበሌ ሪዞርትፕሮጀክት የበጀት ድርሻ ላይ ፣በሸበሌና ቆራሄ ዞኖች የነዳጅ ቁፋሮ በሚከናወኑባቸው ወረዳዎች በሚተገበሩ ልዩ ፕሮጀክቶች ላይ ተወያይቷል።
ምክር ቤቱ የክልሉ ፀጥታ ተቋማትን ማጠናከርና የክልሉ ሠራተኞች አስተዳደርና አገልግሎት አሰጣጥ መልሶ ማደራጃ እንዲሁም ስደትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በተዘጋጁ የአሰራር ማሻሻያዎችና የአዳሪ ትምህርት ቤቶች መመስረቻና አስተዳደር አዋጅ ላይ ተወያይቶ የቀረቡትን አጀንዳዎች አፅድቋል።