የሀገር ውስጥ ዜና

የጥምቀት በዓል በሰላም እንዲከበር ዝግጅት ማድረጉን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፖሊስ ገለጸ

By Melaku Gedif

January 18, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥር 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የከተራና የጥምቀት በዓላት ያለምንም የጸጥታ ስጋት እንዲከበሩ አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጉን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል።

የኮሚሽኑ ም/ ኮሚሽነር አብርሃም ቲርካስ እንደገለጹት፥ የከተራና የጥምቀት በዓላት ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ እሴታቸውን ጠብቀው በሰላም እንዲከበሩ በየደረጃው ባሉት መዋቅሮች ዝግጅት ተደርጓል።

ለዚህም ኮሚቴ ተዋቅሮ የክልሉ ፖሊስ ከአድማ ብተና፣ ከሚሊሻ እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየሰሩ እንደሆነ ነው የገለጹት።

በተለይም በዓላቱ በስፋት በሚከበሩባቸው አካባቢዎች የጸጥታ አካላት ከወጣቶች ጋር ስምሪት በመውሰድ የጸጥታ ጥበቃ ሥራዎች እንደሚከናወኑ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል።

ሕብረተሰቡም በዓሉ ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ በድምቀት እንዲከበር የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ጥሪ አቅርበው፤ የበዓሉን ሰላም የሚያውኩ አጠራጣሪ ሁኔታዎችን ሲመለከትም በአካባቢው ላሉ የጸጥታ አካላት ጥቆማ እንዲሰጥ ጠይቀዋል።

በመላኩ ገድፍ