አዲስ አበባ፣ ጥር 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል የዘንድሮው የተፋሰስ ልማት ሥራ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች እየተካሄደ ነው።
የክልሉ ግብርና ቢሮ ሃላፊ ጌቱ ገመቹ÷ በዛሬው እለት በጅማ ዞን ኦሞ ናዳ ወረዳ ተገኝተው የተፋሰስ ልማት ሥራውን አስጀምረዋል።
በክልሉ ባለፉት አመታት በተሰሩ ስራዎች የከርሰ ምድር ውሃ መጨመሩን በመግለጽ በዚህ የበጋ ወራትም የግብርና ልማት ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል።
በተፋሰስ ልማቱ እርከን ማውጣትን ጨምሮ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች የሚሰሩ ሲሆን÷9 ነጥብ 8 ሚሊየን የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳታፊ እንደሚሆኑ ተገልጿል፡፡
የተፋሰስ ልማት ሥራው በተለያየ ምክንያት የተጎዳ መሬትን ከንክኪ መከለል፣ ምንጭ ማጎልበትና ችግኝ እንክብካቤን ያካትታል ተብሏል፡፡
በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ላይ የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የመንግስት ሰራተኞች፣ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች ተሳትፈዋል፡፡
ዘንድሮ በክልሉ 3 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ የተፋሰስ ልማት፣ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ለማከናወን መታቀዱን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ መግለጻቸው ይታወሳል።
በሙክታር ጣሐ