አዲስ አበባ፣ ጥር 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ታላላቅ የአደባባይ ሁነቶች የጎብኝዎችን ቀልብ በመሳብ ረገድ ትልቅ ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል ሲሉ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ቀጀላ መርዳሳ ገለጹ።
ሚኒስትሩ በአዲስ አበባ ጃንሜዳ እየተከበረ ባለው የጥምቀት በዓል ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት፤ ሀገራችን ኢትዮጵያ ከጥምቀት ባሻገር ሌሎች ታላላቅ የአደባባይ ሁነቶች ባለቤት እንደመሆኗ እነዚህን ሃብቶች በሚገባ መጠበቅና መጠቀም ይገባል ብለዋል።
በዚህም የሀገሪቱን ሰላምና አንድነት በማስጠበቅና የጎብኝዎችን ቀልብ በመሳብ ረገድ ትልቅ ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው አስገንዝበዋል።
የጥምቀት በዓል በማህበረሰቡ ዘንድ ልዩ ቦታ የሚሰጠው እና ሁሉም በጉጉት የሚጠብቀው ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ ደሃ ሃብታም ሳይባል ሁሉም አምሮና ተውቦ ወደ አደባባይ ወጥቶ የሚያከብረው በዓል መሆኑን ገልጸዋል።
በዓሉ በሰዎች መካከል ፍቅርና መደጋገፍ እንዲሁም ወሰን የለሽ ሀሴት የሚታይበት ታላቅ በዓል በመሆኑ መንከባከብ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
እንዲህ ያሉ በዋጋ ሊተመኑ የማይችሉ ታላላቅ እሴቶቻችንን በሚገባ አውቀን ልንጠብቃቸውና ልንከባከባቸው ይገባናል ብለዋል።
እንደዚህ ያሉ ሃብቶች ጎልብተው እንዲዘልቁ መንግስት አቅዶ እየሰራ እንደሆነ ገልጸው፤ በዘርፉ ጥናትና ምርምር የሚያደርጉ ተቋማትና ህዝቡ በጋራ በመሆን ለሃብቶቹ እንክብካቤና ጥበቃ እንዲታደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።