የሀገር ውስጥ ዜና

ከ9 ሚሊየን ብር በላይ መንግስትን አሳጥተዋል የተባሉ በቀረበባቸው የሙስና ወንጀል ክስ የጥፋተኝነት ፍርድ ተላለፈባቸው

By Melaku Gedif

January 22, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥር 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ9 ሚሊየን ብር በላይ ዓመታዊ ግብር ክፍያ መንግስትን አሳጥተዋል የተባሉ ግለሰቦች በቀረበባቸው የሙስና ወንጀል ክስ የጥፋተኝነት ፍርድ ተላለፈባቸው።

የጥፋተኝነት ፍርዱን የሰጠው የኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ወንጀል ችሎት ነው።

ተከሳሾቹ በግል የስራ ተቋራጭ የሆኑት አብይ አማረ ዋሴ እና የኦሮሚያ ገቢዎች ቢሮ የሒሳብ ባለሙያ የነበሩት ተረፈ ቦጃ ናቸው።

የኦሮሚያ ፍትህ ቢሮ የሙስና ጉዳዮች ዐቃቤ ሕግ በተከሳሾቹ ላይ የተሳትፎ ደረጃቸውን ጠቅሶ ሁለት የወንጀል ክሶችን በ2015 ዓ.ም መጨረሻ ባጠቃላይ በ3 ተከሳሾች ላይ ክስ መመስረቱን መዘገባችን ይታወሳል።

ዐቃቤ ሕግ ያቀረበው ክስ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 ንዑስ ቁጥር 1 እና አንቀጽ 33 እንዲሁም ሙስናን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 13 ንዑስ ቁጥር 2 ላይ የተመላከተውን ድንጋጌና የታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 203/2009 አንቀጽ 118 ንዑስ ቁጥር 1 ስር የተመላከተውን ድንጋጌ ተላልፈዋል የሚል ነበር።

በዚህም በአንደኛ ክስ በሁሉም ተከሳሾች ላይ የቀረበ ሲሆን በሁለተኛው ክስ ላይ ደግሞ በአንደኛ ተከሳሽ ላይ ብቻ ነው የቀረበው።

በዚህም ክስ እንደተመላከተው 1ኛ ተከሳሽ የታክስ አስተዳደር አዋጁን በመተላለፍ ዓመታዊ የግብር ገቢ መክፈል ሲገባቸው የከፈሉ ለማስመሰል ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጠመንጃ ያዥ ቅርንጫፍ የተሰጠ የሚመስል ሀሰተኛ የኦሮሚያ ገቢዎች ሒሳብ ያልሆነ የባንክ ስሊፕ ማቅረባቸው ተመላክቷል፡፡

2ኛ እና 3ኛ ተከሳሾች ደግሞ ከ1ኛ ተከሳሽ ጋር በመመሳጠር ያቀረቡትን ሐሰተኛ የባንክ ስሊፕ ሕጋዊነት እና የሌሎች ሰነዶችን ትክክለኛነት ሳያረጋግጡ በመቀበል የገቢ ግብር ከፍለዋል በማለት የገቢ ደረሰኝ መስጠታቸው ተጠቅሷል፡፡

ከዚህ በኋላ ደግሞ ስራ ተቋራጩ ዓመታዊ ግብር ከነቅጣቱ እንደከፈለ በማስመሰል ዓመታዊ ግብር ባለመክፈላቸው ምክንያት የተጣለባቸው የንብረት እግድ እንዲነሳላቸው በ3ኛ ተከሳሽ በኩል ለህግ ክፍል መጻፉ በክሱ ተጠቅሷል።

በአጠቃላይ ተከሳሾቹ መንግስትን 9 ሚሊየን 292 ሺህ 127 ብር ከ83 ሳንቲም ገቢ አሳጥተዋል በማለት ዐቃቤ ሕግ ክስ አቅርቦባቸዋል።

ተከሳሾቹ የቀረበባቸው ክስ ዝርዝር ደርሷቸውና በችሎት በንባብ ከተሰማ በኋላ ዝርዝሩ ላይ የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊት አለመፈጸማቸውን ጠቅሰው የዕምነት ክህደት ቃላቸው በመስጠታቸው ዐቃቤ ሕግ የሰው ምስክሮችንና የሰነድ ማስረጃዎችን አቅርቧል።

የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን የመረመረው ፍርድ ቤቱ ተከሳሾቹ በተከሰሱበት ድንጋጌ እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቶ ተከሳሾቹ የመከላከያ ማስረጃ ያቀረቡ ሲሆን 1ና 2ኛ ተከሳሾች ባቀረቡት የመከላከያ ማስረጃ የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን በተገቢው አላስተባበሉም በማለት ፍርድ ቤቱ የጥፋተኝነት ፍርድ ሰጥቷል።

በዚሁ መዝገብ 1ኛ ተከሳሽ ዓመታዊ ግብር ባለመክፈላቸው ምክንያት የተጣለባቸው የንብረት ዕግድ እንዲነሳላቸው ለህግ ክፍል ደብዳቤ በመጻፍ ዕግዱን አስነስቷል ተብሎ ተከሶ የነበረው የኦሮሚያ ገቢዎች ቢሮ የቀድሞ የግብር ክትትል ቡድን መሪ መንግስቱ ሙሉነህ በሚመለከት ግን ፍርድ ቤቱ የቀረበውን ማስረጃ ተከላክሏል ብሎ በነጻ አሰናብቶታል።

በነጻ የተሰናበተውን ተከሳሽን በሚመለከት ዐቃቤ ሕግ ይግባኝ እንደሚጠይቅ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ገልጿል።

በታሪክ አዱኛ