የሀገር ውስጥ ዜና

በመዲናዋ የጥምቀት በዓል በድምቀት ተከብሮ መጠናቀቁን የአዲስ አበባ ከተማ ሀገረ ስብከት አስታወቀ

By Feven Bishaw

January 23, 2024

 

አዲስ አበባ፣ ጥር 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ)በአዲስ አበባ የጥምቀት በዓል በድምቀት ተከብሮ መጠናቀቁን የአዲስ አበባ ከተማ ሀገረ ስብከት አስታውቋል፡፡

በዓሉ ጃንሜዳን ጨምሮ በ78 ጥምቀተ ባህራት በሁሉም ክፍለ ከተሞች በድምቀት ተከብሮ መጠናቀቁን ሀገረስብከቱ በሰጠው መግለጫ ገልጿል።

በከተማው የከተራ፣ የጥምቀት እና የቃና ዘገሊላ በዓላት ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን ጠብቆ መከበሩን የገለፁት የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሄኖክ ከ260 በላይ አድባራት እና ታቦታት ከ6 እስከ 7 ሚሊየን በሚገመቱ ምዕመናን ታጅበዉ ከመንበራቸው ወደ ጥምቀተ ባህራት ደርሰው ተመልሰዋል ብለዋል ።

በዓሉ በድምቀት ተከብሮ እንዲጠናቀቅ የደንብ ማስከበር አባላት ከጸጥታ አካላት፣ከሀይማኖት አባቶች፣ ከከተማው ነዋሪዎች እና ከበጎ-ፍቃደኛ ወጣቶች ጋር በመቀናጀትና በመናበብ ውጤታማ ስራዎች መስራታቸውን የገለፁት ብፁዕ አቡነ ሄኖክ ለዚህም የከተማ አስተዳደሩን ጨምሮ አስተዋፅኦ ላበረከቱ አካላት ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በምንተስኖት ሙሉጌታ