የሀገር ውስጥ ዜና

ከኃይል ሽያጭ ከ12 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር በላይ ተገኘ

By ዮሐንስ ደርበው

January 24, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥር 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ አጋማሽ ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ ከቀረበ የኃይል ሽያጭ 12 ቢሊየን 848 ሚሊየን 139 ሺህ 990 ብር መገኘቱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ፡፡

ከኃይል ሽያጭ 13 ቢሊየን 473 ሚሊየን 246 ሺህ 943 ብር ለማግኘት ታቅዶ÷ ከሀገር ውስጥ የኃይል ሽያጭ 10 ቢሊየን 234 ሚሊየን 869 ሺህ 88 እንዲሁም ለውጭ ሀገራት ከተሸጠ ኃይል 2 ቢሊየን 613 ሚሊየን 270 ሺህ 902 ብር መገኘቱ ተጠቅሷል፡፡

ከኢትዮጵያ የኃይል ምርቱን የገዙ የውጭ ሀገራትም÷ ጅቡቲ፣ ሱዳን እና ኬንያ መሆናቸው ተብራርቷል፡፡

የግማሽ ዓመቱ አፈጻጸምም 95 ነጥብ 36 በመቶ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ሞገስ መኮንን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ገልጸዋል፡፡

በግማሽ ዓመቱ ለማምረት የታቀደው ኃይል 10 ሺህ 788 ጊጋ ዋት ሰዓት መሆኑን እና 9 ሺህ 549 ነጥብ 2 ጊጋ ዋት ሰዓት ማምረት መቻሉንም ጠቅሰዋል፡፡

ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በኃይል የ1 ሺህ 317 ነጥብ 5 ጊጋ ዋት ሰዓት ወይም የ13 ነጥብ 79 በመቶ ብልጫ ማሳየቱን ነው የገለጹት፡፡

ለመሸጥ የታቀደው 8 ሺህ 505 ጊጋ ዋት ሰዓት መሆኑን አስታውሰው÷ 7 ሺህ 788 ጊጋ ዋት ሰዓት መሸጡን አረጋግጠዋል፡፡

አፈጻጸሙ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸርም የ8 ነጥብ 5 በመቶ ዕድገት አለው ነው ያሉት፡፡

በዮሐንስ ደርበው