የሀገር ውስጥ ዜና

አስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ ለሚሹ ወገኖች ድጋፍ ለማዳረስ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

By ዮሐንስ ደርበው

January 25, 2024

የአገልግሎቱ ሚኒስትር ዴዔታ ሰላማዊት ካሳ በሰጡት መግለጫ÷በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተከሰተውን የዝናብ እጥረት ተከትሎ በተለይም ከዚህ ቀደም በድርቁ ተጎጂ በነበሩ አካባቢዎች ያሉ ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ እንደሚሹ ተናግረዋል፡፡

ለእነዚህ ዜጎች የሰብዓዊ እርዳታ ለማዳረስም መንግስት ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

በ2016 በጀት ዓመት መጀመሪያ ጀምሮ እስከ ታህሳስ ወር ድርስም ከመንግስት እና ከአጋር አካላት በተገኘ 15 ቢሊየን ብር በ3 ዙሮች አስቸኳይ የሰብዓዊ ድጋፍ ለሚሹ ዜጎች ድጋፍ እንዲያገኙ ሲሰራ ቆይቷል ብለዋል፡፡

በዚኅም በመጀመሪያ ዙር ለ7 ነጥብ 3 ሚሊየን ወገኖች እና በ2ኛው ዙር ደግሞ ለ3 ነጥብ 6 ሚሊየን ወገኖች አስቸኳይ የሰብዓዊ ድጋፍ ማድረስ ተችሏል ነው ያሉት፡፡

ለ6 ነጥብ 5 ሚሊየን ዜጎች ደግሞ በሶስተኛው ዙር የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲደርሳቸው መደረጉን አመላክተዋል፡፡

የድጋፍ አይነቶቹም 1 ነጥብ 7 ሚሊየን ኩንታል የሚሆን የምግብ ድጋፍ በተለይ በድርቅ ተጎጂ ሆነው አስቸኳይ ድጋፍ ለሚሹ ድጋፉ መደረጉን አንስተዋል፡፡

በጥሬ ገንዘብም ድጋፍ መደረጉን ያነሱት ሚኒስትር ዴዔታዋ÷ የአካባቢው ገበያ ተጠንቶ በአካባቢያቸው ያለውን ምግብ ገዝተው እንዲጠቀሙ 2 ቢሊየን ብር ድጋፍ ተደርጓል ብለዋል፡፡

ከተደረገው የምግብ ድጋፍ 77 በመቶ የሚሆነውን መንግስት የሸፈነ ሲሆን÷ ይህም ወደ 11 ቢሊየን ብር የሚገመት ድጋፍ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

23 በመቶ የሚሆነውን ድግሞ የተለያዩ ዓለም አቀፍ አጋር አካላት ያደረጉት ድጋፍ መሆኑን ገልጸው÷ ይህም 4 ቢሊየን ብር አካባቢ መሆኑን አንስተዋል፡፡

በጥሬ ገንዘብ የተሰራጨው ብርም በአማራ ፣ኦሮሚያ፣ ሶማሌ ፣ ትግራይ፣ ደቡብ ኢትዮጵያ፣ አፋር፣ ሐረሪ እና ድሬዳዋ ክልሎች የተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የተሰራጨውን የጥሬ ብር ድጋፍ 40 በመቶ መንግስት 60 በመቶ ቀጥታ ከዓለም ባንክ የተገኘ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በፌቨን ቢሻው