አዲስ አበባ፣ ጥር 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የመንግስት ት/ቤቶች መምህራን በህብረት ስራ ማህበራት ተደራጅተው የቤት ባለቤት እንዲሆኑ ለማስቻል እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ፡፡
በከተማ አስተዳደሩ በሚገኙ የመንግስት ትምህርት ቤቶች ለሚያስተምሩ መምህራን የጋራ መኖሪያ ህንጻ በህብረት ስራ በማደራጀት ግንባታ ለማስጀመር በተዘጋጀ ሰነድ ዙሪያ ውይይት ተካሂዷል።
በውይይት መድረኩ የአስተዳደሩ ትምህርት ቢሮና የአዲስ አበባ መምህራን ማህበር አመራሮችን ጨምሮ የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት የስራ ሃላፊዎች እንዲሁም የህብረት ስራ ኮሚሽን አመራሮችና የክፍለ ከተማ ትምህርት ጽ/ ቤት ሃላፊዎች ተሳትፈዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ም/ሃላፊ አቶ አሊ ከማል ÷ ከተማ አስተዳደሩ የመምህራንን የቤት ጥያቄ ለመመለስ የተለያዩ አማራጮችን በመከተል ላይ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
ከእነዚህ አማራጮች መካከል አንዱ መምህራንን በህብረት ስራ ማህበራት በማደራጀት የቤት ባለቤት እንዲሆኑ ማስቻል ነው ብለዋል፡፡
የውይይት መድረኩ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር የጋራ ግንዛቤ በመያዝ ወደ ተግባር ለመግባት የሚያግዝ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የከተማ አስተዳደሩ መምህራን ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ድንቃለም ቶሎሳ በበኩላቸው÷የከተማ አስተዳደሩ ባፀደቀው መመሪያ መሰረት መምህራን ተደራጅተው የቤት ባለቤት እንዲሆኑ ማህበሩ ከባለድርሻ አካላት ጋር የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱን ተናግረዋል፡፡
በቀጣይ የቀረበውን የማስፈጸሚያ ሰነድ መሰረት በማድረግ በአስቸኳይ ወደ ተግባር የሚገባ መሆኑን ነው ያስታወቁት፡፡
መምህራኑ በቀረቡላቸው አማራጮች መሰረት የቁጠባ ባህላቸውን በማሳደግ በህብረት ስራ ማህበር ተደራጅተው የባለ 1፣ ባለ 2 እና የባለ 3 መኝታ ቤት ባለቤት እንዲሆኑ መታቀዱ ተጠቁሟል፡፡
ለዚህም የቅድመ ዝግጅት ስራ ተጠናቆ ወደ ተግባር ለመግባት በእንቅስቃሴ ላይ መሆናቸውን የህብረት ስራ ኮሚሽን እንዲሁም የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ አመራሮች መግለጻቸውን የቢሮው መረጃ ያመላክታል፡፡