የሀገር ውስጥ ዜና

በ22 ነጥብ 77 ቢሊየን ብር የመንገድ ግንባታና ጥገና ሥራ ተከናወነ

By ዮሐንስ ደርበው

January 26, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥር 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ አጋማሽ በ22 ነጥብ 77 ቢሊየን ብር ወጪ የመንገድ ግንባታና ጥገና ሥራ መከናወኑን የኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር አስታወቀ፡፡

በአሥተዳደሩ የፕላንና ፕሮግራም ማኔጅመንት ዳይሬክተር ቆንጂት ዓለሙ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት÷ በግማሽ ዓመቱ 402 ኪሎ ሜትር አዲስ መንገድ ለመገንባት ታቅዶ 279 ኪሎ ሜትር ተገንብቷል፡፡

ይህን ተከትሎም የፌደራል መንገዶችን ሽፋን 30 ሺህ 456 ኪሎ ሜትር ማድረስ ተችሏል ነው ያሉት፡፡

እንዲሁም 101 ኪሎ ሜትር የነባር መንገዶች ማጠናከርና የነባር መንገዶች ደረጃ ማሻሻል ሥራ መከናወኑን ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል 4 ሺህ 519 ኪሎ ሜትር መንገድ መጠገኑን እና ከዚህ ውስጥ 85 ኪሎ ሜትሩ ከባድ ጥገና መሆኑን አብራርተዋል፡፡

4 ሺህ 434 ኪሎ ሜትሩ ደግሞ ወቅታዊና መደበኛ ጥገና መሆኑን ነው ያስታወቁት፡፡

በተለያዩ አካባቢዎች የሚስተዋለው የፀጥታ ችግር የበጀት ዓመቱ አፈፃፀም ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩንም ተናግረዋል፡፡

በ2016 በጀት ዓመትም 945 ኪሎ ሜትር አዲስ መንገድ ለመገንባት መታቀዱን አመላክተዋል፡፡

በዮሐንስ ደርበው