አዲስ አበባ፣ ጥር 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል ከነገ ጀምሮ በሁሉም አካባቢዎች የወጣቶች የሰላም ኮንፈረንስ እንደሚካሄድ የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ገለጸ፡፡
የክልሉ ቢሮ ኃላፊ አቶ ርዚቅ ኢሳ÷በወጣቶች የሰላም ኮንፈረንስ ከቀበሌ፣ ክፍለ ከተማና ወረዳዎች የተውጣጡ ከ 1 ነጥብ 7 ሚሊየን በላይ ወጣቶች እንደሚሳተፉ ተናግረዋል።
ወጣቶች የሀገራቸውን ባህል፣ እሴትና ብሔራዊ ጥቅም በአግባቡ በመረዳት በአንድነት ሊቆሙ እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡
በሰላም ኮንፈረሱ መሳተፍ የክልሉን የሰላምና የልማት ጉዞ ወደነበረበት ለመመለስ ከማገዝ በተጨማሪ የጋራ ሃገራዊ ማንነትና እሴት የተላበሰ ወጣት ለመፍጠር የሚደረገውን ሃገራዊ ጥረትም ያግዛል ብለዋል።
የወጣቶች የሰላም ኮንፈረንስ”አድዋ ለዘላቂ ሰላምና ጠንካራ ሃገረ መንግሥት ግንባታ” በሚል መሪ ሃሳብ እየተካሄደ የሚገኘው ሃገር አቀፍ የወጣቶች መድረክ አካል ነውም ተብሏል፡፡
በአማራ ክልልም ወጣቶች ታሪካቸውን፣ ባህላቸውንና በጎ እሴቶቻቸውን በመረዳት ለዘላቂ ሰላምና ሃገረ መንግሥት ግንባታ የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ ለማስቻል ያለመ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
በደሳለኝ ቢራራ