አዲስ አበባ፣ ጥር 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ የህዝብ እና ቤት ቆጠራ ለማድረግ እቅድ መያዙን የፕላንና ልማት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ሚነስቴሩ በቀጣይ ሶስት ዓመታ የሚተገበረዉ የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ ልማት ፕሮግራም ይፋ አድርጓል፡፡
በፕሮግራሙ መሰረትም በሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት የኢኮኖሚ ቆጠራ፣ የግብርና እንዲሁም የህዝብና ቤት ቆጠራ ለማድረግ እቅድ መቀያዙ ተገልጿል፡፡
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር)÷ በፕሮግራሙ የሚደረገዉ የግብርና ቆጠራ አዲስ በግብርና ስርአቱ ዉስጥ የገቡ የበጋ የስንዴ ልማትን ጨምሮ የተደራጀ የግብርና ዘርፍ መረጃ እንዲኖር ያደርጋል ብለዋል፡፡
በተጨማሪም የህዝብና ቤት ቆጠራ ለማድረግ መንግስት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለው ገልጸው÷ በዓለም አቀፍ መስፈርት መሰረት ቆጠራዉን ለማድረግ የሚያስችሉ አመቺ ሁኔታዎች ባለመኖራቸዉ እስካሁን ቆጠራውን ማካሄድ እንዳልተቻለ ገልጸዋል።
በሀገሪቱ ተከስቶ የነበረው የፀጥታ ችግር የህዝብ ቆጠራ እንዳይካሄድ ምክንያት መሆኑ የተገለፀ ሲሆን የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ወደ ሰላም መምጣቱና የአማራ ክልልን ጨምሮ ሌሎች አካባቢዎችም ያለዉ የሰላም ሁኔታ እየተሻሻለ በመምጣቱ እቅዱ በፕሮግራሙ ዉስጥ መቀመጡን ተገልጿል፡፡
የህዝብ ቆጠራዉን ለማከናወን ከፍተኛ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች የሚጠይቅ በመሆኑም የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ተጀምረዋል መባሉን ከፕላንና ልማት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡