አዲስ አበባ፣ ጥር 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከቤኒሻጉል ጉሙዝ እንዲሁም ክልሉ ከሚዋሰንባቸው የኦሮሚያና አማራ ክልሎች በጸጥታ ችግር ተፈናቅለው በመጠለያ ጣቢያ ከነበሩ 475 ሺህ 385 ተፈናቀዮች 455 ሺህ 949 ያህሉ ወደ ቀያቸው መመለሳቸው ተገለጸ፡፡
የክልሉ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር መሐመድ አብዱላአዚዝ በሰጡት መግለጫ÷ ባለፉት ዓመታት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በአጎራባች የኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች አካባቢዎች ተፈጥሮ በነበረው የፀጥታ ችግር 475 ሺህ 385 መፈናቀላቸውን አስታውሰዋል፡፡
ከአንድ ዓመት ወዲህ በተፈጠረው መረጋጋትም 455 ሺህ 949 ዜጎች ወደ ቀያቸው ተመልሰው መደበኛ ኑሯቸውን እንደቀጠሉ አንስተዋል፡፡
ቀሪዎቹ 34 ሺህ 507 ተፈናቃዮች በክልሉ በሚገኙ ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች እንደሚገኙ ገልጸው፤ እነዚህን ወገኖች በዘላቂነት ለማቋቋም እየተሠራ መሆኑን መናገራቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ አመላክቷል፡፡
ወደ ቀያቸው የተመለሱ ዜጎችን በዘላቂነት መልሶ ለማቋቋም እየተሠራ መሆኑን ገልጸው÷ ትምህርት ቤት፣ የጤናና የውሃ ተቋማት ተገንብተው አገልግሎቶች እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
ከፌደራል እና ከተባባሪ ድርጅቶች የሚደረጉ ድጋፎችን ወደ ክልሉ ለማስባት በአጎራባች ክልል ያለው የፀጥታ ችግር እንቅፋት እንደሆነባቸውም በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡
በክልሉ በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ዜጎችንም ሆነ ወደ ቀያቸው የተመለሱትን መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ርብርብ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡