አዲስ አበባ፣ ጥር 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ260 ኬሻ በላይ ቡና በህገ ወጥ መንገድ አከማችተው ለመሸጥ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ገለጸ፡፡
ተጠርጣሪዎቹ ቡና ለመሸጥ የሚያስችል ምንም አይነት ሕጋዊ ፈቃድ እንደሌላቸው የገለጸው ፖሊስ÷ በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ ፉሪ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኝ አንድ መጋዘን ውስጥ ቡና ስለማከማቸታቸው መረጃና ጥቆማ እንደደረሰውና ክትትል ማድረግ መጀመሩን ጠቅሷል፡፡
ቡናውን የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3- A10225 ኢት በሆነ ተሽከርካሪ ጭነው ወደ ሌላ ቦታ ወስደው ለመሸጥ ሲንቀሳቀሱ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 2 አያት አካባቢ በቁጥጥር ስር እንደዋሉም ተገልጿል፡፡
የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የልዩ ልዩ ወንጀል ምርመራ ክፍል ከኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለስልጣን ባገኘው መረጃ መሰረት ተጠርጣሪዎቹ ምንም አይነት ፍቃድ እንደሌላቸው ተጠቁሟል፡፡
በቁጥጥር ስር የዋለው 267 ኬሻ ቡና በፍርድ ቤት ትዕዛዝ መሰረት ለኢትዮጵያ ምርት ገበያ ገቢ እንዲሆን ተወስኗልም ነው የተባለው፡፡
በተጠርጣሪዎቹ ላይም ምርመራ እየተካሄደ ሲሆን÷ ሕገ- ወጥ ተግባራትን ለመከላከል የህብረተሰቡ ተባባሪነት ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ፖሊስ አስገንዝቧል።