የሀገር ውስጥ ዜና

አቶ አሕመድ ሽዴ የልማት ባንክ አፈጻጸም ውጤት የተመዘገበበት መሆኑን ገለጹ

By Shambel Mihret

February 07, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥር 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ አጋማሽ አፈጻጸም ጥሩ ውጤት የተመዘገበበት መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አሕመድ ሽዴ ገለጹ፡፡

የባንኩ የስድስት ወራት አፈጻጸም የገንዘብ ሚኒስቴር፣ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳርና ተጠሪ ተቋማት በተገኙበት ግምገማ ተካሂዷል፡፡

በመድረኩ አቶ አሕመድ ሽዴ እንዳሉት÷ የባንኩ አሰራር በየጊዜው እየተሻሻለ ከመምጣቱ ባሻገር የፋይናስ ቁመናው ጤናማ ነው፡፡

በተለይም በግብርናው ዘርፍ የነበሩ ችግሮችን በማረም ውጤት የመጣበት መሆኑ የሚበረታታ መሆኑን ጠቅሰው÷ በቀጣይም በሁሉም ዘርፎች ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ለማሳደግ ያሉትን አማራጮች በሙሉ መጠቀምና የባንኩን የሀብት ደረጃ ማሳደግ እንደሚገባ የገለጹት ደግሞ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ኃይለሚካኤል ናቸው፡፡

የባንኩን የብድር አሰባሰብ ስርዓት ዘላቂ እንዲሆን ለማስቻል ልምዱ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡

የልማት ባንክ ፕሬዚዳንት ዮሐንስ አያሌው (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ ባንኩ በአምስት ዓመቱ የስትራቴጂክ እቅዱ ያስቀመጣቸውን ስራዎች በመለየት መፈጸም መቻሉ ለስኬት እንዳበቃው ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይ የብድር ስርጭቱ ከዕቅድ በላይ እንደተፈጸመ በመግለጽ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ አፈጻጸም ጋር ሲነጻጸር ብልጫ ማስመዝገቡንም አመላክተዋል፡፡

በቀጣይም የስትራቴጂክ እቅዱ የመጨረሻ ምዕራፍ ትግበራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና የመጭው አምስት ዓመት አዲስ እቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ስራ እንደሚገባም መገለጹን ከልማት ባንክ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡