የሀገር ውስጥ ዜና

ፍርድ ቤቶች የሚሰጡትን አገልግሎት ለማሻሻል እራሳቸውን ብቁ ማድረግ አለባቸው – አፈ-ጉባዔ ታገሰ ጫፎ

By Feven Bishaw

February 10, 2024

 

አዲስ አበባ፣ የካቲት 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ፍርድ ቤቶች ለሕዝቡ የሚሰጡት አገልግሎት የተሻለ ለማድረግ በሰው ኃይል፣ ጊዜውን በዋጀ ቴክኖሎጂና በምቹ መሰረተ ልማት እራሳቸውን ብቁ ማድረግ እንዳለባቸው የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አፈ-ጉባዔ ታገሰ ጫፎ ገለጹ።

ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አዲስ ዋና መሥሪያ ቤት በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ ተክለ ኃይማኖት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ለመገንባት ዛሬ የመሠረተ ድንጋይ ተቀምጧል።

አፈ-ጉባዔ ታገሰ ጫፎ፣ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ቴዎድሮስ ምህረትና የከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ሌሊሴ ደሳለኝ የሕንጻ ግንባታውን የመሰረት ድንጋይ አስቀምጠዋል።

አፈ-ጉባዔ ታገሰ ጫፎ በዚህ ጊዜ እንደገለጹት÷ ፍ/ቤቶች ለሕዝቡ የሚሰጡት አገልግሎት የተሻለ ለማድረግ በሰው ኃይል ጊዜውን በዋጀ ቴክኖሎጂና በምቹ መሰረተ ልማት እራሳቸውን ብቁ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

ከዚህ አንጻር በዛሬውም ዕለት የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠለት የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ ቤት ዋና መሥሪያ ቤት ግንባታ ለኅብረተሰቡ ምቹና ቀልጣፋ የሕግ አገልግሎት ለመስጠት ከፍተኛ አቅም እንደሚፈጥር መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ለፍርድ ቤቶች ምቹ የሥራ አካባቢን መፍጠር ብቻ የሕዝብን የፍትህ ጥያቄ ሙሉ በሙሉ የሚመልስ አለመሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋልም ነው ያሉት አፈ ጉባዔው፡፡

የፍርድ ቤት አመራሮችና ባለሙያዎች እራሳቸውን በክህሎትና በእውቀት ማጎልበት እንዳለባቸው እና በሥነ-ምግባር የተመሰከረላቸው አገልጋዮች ሊሆኑ እንደሚገባም ተናግረዋል።

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ቴዎድሮስ ምህረት በበኩላቸው÷የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዋና መሥሪያ ቤት ሕንጻን መገንባት በዘርፉ ላይ ከመሰረተ ልማት ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዝ ገልጸዋል።