አዲስ አበባ፣ የካቲት 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት ሀገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ሰላም የማስፈን እንቅስቃሴ ላይ ያተኮረ ጉባዔ በመቀሌ ከተማ እየተካሄደ ነው።
በውይይት መድረኩ የሰላም ሚኒስትር ዴዔታ ከይረዲን ተዘራ (ዶ/ር) ፣ በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የእቅድ እና ማህበራዊ ልማት ካቢኔ ሴክሬታሪያት ክንደያ ገ/ሕይወት (ፕ/ር) እና የመቀሌ ከተማ ከንቲባ ኤልያስ ካሕሳይ ተገኝተዋል፡፡
እንዲሁም የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፋና ሃጎስ (ዶ/ር) ፣ የፌዴራል እና የክልል አመራሮች፣ የሃይማኖት አባቶች እንዲሁም የተፈናቃይ ወገኖች ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡
ውይይቱ በዋናነት ሕብረተሰቡ ለሚያነሳቸው የልማት፣ የመልካም አስተዳደር፣የሰላምና ጸጥታ እንዲሁም ሌሎች ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ያስችላል ተብሏል፡፡ የሰላም ሚኒስትር ዴዔታ ከይረዲን ተዘራ (ዶ/ር)÷ሚኒስቴሩ የሰላምን ዘላቂነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ሥራዎችን ከማህበረሰብ ጀምሮ በየደረጃው እያከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት መሰረት በማስያዝ ረገድ መቀሌ ዩኒቨርሲቲ የወሰደውን ተነሳሽነትም አድንቀዋል፡፡
ክንደያ ገ/ሕይወት (ፕ/ር) በበኩላቸው በትግራይ ክልል በጦርነቱ ሳቢያ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል ያሉ ሲሆን÷መሰል ተግባር በሌሎች አካባቢዎች እንዲፈጠር አንፈልግም ብለዋል፡፡
በዚህም አሁን ያለውን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ ዘርፈ ብዙ የመልሶ ግንባታ ሥራዎች መስራት እንዲሁም ስለ ሰላም እና እርቅ መስበክ ከዩኒቨርሲቲዎች ይጠበቃል ነው ያሉት፡፡
ችግሮችን በሰለጠነ መንገድ በሰላም የመፍታት አካሄድ ለማዳበር ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንደሚገባውም አስገንዝበዋል፡፡
በመድረኩ የተለያዩ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት የተካሄደባቸው ሲሆን÷ ጉበዔው ለተከታታይ ሁለት ቀናት እንደሚቆይ ተጠቁሟል።
በሲሳይ ሃዱሽ