የሀገር ውስጥ ዜና

አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸኃፊ የሱዳን ልዩ መልዕክተኛ ጋር ተወያዩ

By Amele Demsew

February 13, 2024

አዲስ አበባ፣ የካቲት 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸኃፊ የሱዳን ልዩ መልዕክተኛ ራምታኒ ላማምራ ጋር ተወያዩ፡፡

በውይይታቸውም አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ÷ራምታኔ ላማምራ የሱዳን ልዩ መልዕክተኛ ሆነው በመሾማቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው በሱዳን የተከሰተው ጦርነት ሊቆም እና ግጭቶች በውይይት ሊፈቱ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በሱዳን ያለውን ግጭት ለማስቆም በቀጣናው ያሉ ሀገራት በኢጋድ በኩል የተጠናከረ ጥረት ሊያደርጉ እንደሚገባም ገልጸዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸኃፊ የሱዳን ልዩ መልዕክተኛ ራምታኒ ላማምራ በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ በቀጣናው ግጭቶች በሰላም እንዲፈቱ የምታደርገውን ገንቢ ሚና ማድነቃቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡