አዲስ አበባ፣ የካቲት 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) መቀመጫውን አዲስ አበባ ያደረገው የደቡባዊ ትብብር ድርጅት እውቀትን ለማፍለቅ እና ተደራሽ ማድረግ የሚያስችል የመረጃ ቋት በሳይንስ ሙዚዬም አስመርቋል፡፡
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴዔታ ባይሳ በዳዳ (ዶ/ር)÷ ቴክኖሎጂው የደቡባዊ ትብብር አባል ሀገራትና ተባባሪ ድርጅቶች እውቀትንና ቴክኖሎጂዎችን በጽሑፍ፣ በድምጽና በተንቀሳቃሽ ምስል በነጻ የሚያገኙበት ትልቅ ማዕቀፍ መሆኑን አንስተዋል።
ቴክኖሎጂው የደቡባዊ ሀገራት የዕውቀትና ቴክኖሎጂ ተቀባይና ተጠቃሚ አድርጎ የማሰብን የቆየ እይታ ፈጽሞ የቀየረ ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡
የምርምር ተቋማት፣ ዩኒቨርሲቲዎች፣ መምህራና ተመራማሪዎች እንዲሁም ሌሎች ይህንን ሃብት በኃላፊነት በመጠቀም ለሀገራቸው ዕድገት የበኩላቸውን እንዲያበረክቱም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የደቡባዊ ትብብር ድርጅት ዋና ጸሃፊ ሼህ ማንሱር ቢን ሙሰላም በበኩላቸው÷ አዲሱ ቴክኖሎጂ በድርጅታቸው ለምቶ አገልግሎት ላይ መዋሉ ለአባል ሀገራቱና ተባባሪ ድርጅቶች ትልቅ ሃብት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ቴክኖሎጅውን በመጠቀም ለሀገራቱ የልማት ሥራ ማዋል ይገባል ማለታቸውንም የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡
የድርጅቱ ምክትል ዋና ጸሐፊ ሹመቴ ግዛው (ዶ/ር)÷ የቴክኖሎጂ ውጤቱ አካታችነትን ማዕከላዊ ያደረገ ዘርፍ ተሻጋሪ፣ አካዳሚክ እና አካዳሚካው ያልሆኑ እውቀት ምንጮችን በማቀራረብ ተደራሽነትን የሚያሰፋ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም የደቡባዊ ሀገራት ትብብርን የሚያበረታታ የቴክኖሎጂ ውጤት መሆኑን አብራርተዋል፡፡