አዲስ አበባ፣ የካቲት 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የድርጅት ጥበቃን በጦር መሳሪያ አስፈራርተው ጥቅል ኤሌክትሪክ ገመዶችን ሰርቀዋል የተባሉ ተከሳሾች በ7 እና በ9 ዓመት ጽኑ እስራት ተቀጡ።
የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ቦሌ ምድብ 4ኛ ወንጀል ጉዳዮች ችሎት በተከሳሾች ኤፍሬም አብርሃም እና በአረጋዊ ኪሮስ ላይ በተከሰሱበት የከባድ ውንብድና ወንጀል የቅጣት ውሳኔ ወስኗል።
የፍትህ ሚኒስቴር ቦሌ ምድብ ዐቃቤ ህግ በተከሳሾቹ ላይ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀጽ 32 ንዑስ ቁጥር 1 (ሀ) እና አንቀጽ 671 ንዑስ ቁጥር 1 ለ ስር የተመላከተውን ድንጋጌ ተላልፈዋል በማለት ክስ አቅርቦባቸዋል።
በክሱ ዝርዝር ላይ እንደተመላከተው ተከሳሾቹ ተገቢ ያልሆነ ብልጽግና ለራሳቸው ለማግኘት ወይም ለሌሎች ለማስገኘት በማሰብ በ2015 ዓ.ም በለሚ ኩራ ክ/ከተማ ወረዳ 4 ጌቱ አደባባይ 40/60 ኮንዶሚኒየም ብሎክ 10 ተብሎ በሚጠራ አካባቢ የሚገኝ ቲኤንቲ የተባለ የግል ድርጅት ውስጥ ሌሊት ሚኒባስ ተሽከርካሪ፣ ሽጉጥና ክላሽ መሳሪያ ይዘው ገብተዋል።
ወደ ድርጅቱ ውስጥ ከገቡ በኋላ የድርጅቱን ጥበቃ በያዙት ጦር መሳሪያ በማስፈራራትና በመደብደብ እራሳቸውን እንዳይከላከሉ በማድረግ የድርጅቱን ንብረት ክፍል ሰብረው በመግባት 48 ጥቅል የኤሌክትሪክ ገመድ አውጥተው ከወሰዱ በኋላ በፖሊስ ክትትል በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተከትሎ በከባድ ውንብድና ወንጀል ክስ ተመስርቶባቸዋል።
ተከሳሾቹ ክሱ በችሎት ከደረሳቸው በኋላ የወንጀል ድርጊቱን አለመፈጸማቸውን ጠቅሰው የዕምነት ክህደት ቃላቸውን መስጠታቸውን ተከትሎ ዐቃቤ ህግ የሰውና የሰነድ ማስረጃ አቅርቦባቸዋል።
ፍርድ ቤቱም የዐቃቤ ህግ ማስረጃን መርምሮ እንዲከላከሉ ብይን የሰጠ ቢሆንም ተከሳሾቹ መከላከል ባለመቻላቸው በተከሰሱበት ድንጋጌ የጥፋተኝነት ፍርድ ተላልፎባቸዋል።
ከዚህም በኋላ ዐቃቤ ህግ ቅጣቱ ከብዶ እንዲጣል የቅጣት ማክበጃ አስተያየት ያቀረበ ሲሆን÷ ተከሳሾቹም የተለያዩ የቅጣት ማቅለያ አስተያየቶችን በጽሁፍ አቅርበዋል።
ፍርድ ቤቱ መርምሮ ተከሳሾቹ ያቀረቡትን ሁለት ሁለት የቅጣት ማቅለያ አስተያየት ይዞላቸዋል፤ ዐቃቤ ህግ ያቀረበው የቅጣት ማክበጃ ግን አልተያዘም።
በዚህም መነሻ ፍርድ ቤቱ በዕርከን 28 መሰረት 1ኛ ተከሳሽን በ9 ዓመት ጽኑ አስራት እንዲቀጣ የወሰነ ሲሆን 2ኛ ተከሳሽን ደግሞ በ7 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኗል።
በታሪክ አዱኛ