የሀገር ውስጥ ዜና

የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ርብርብ ያስፈልጋል – ወ/ሮ አይናለም ንጉሴ

By Shambel Mihret

February 15, 2024

አዲስ አበባ፣ የካቲት 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአርባ ምንጭ ከተማን ዕድገት ለማፋጠንና ከአገልግሎት ጋር በተያያዘ የሚታዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ርብርብ እንደሚያስፈልግ የገቢዎች ሚኒስትር ወ/ሮ አይናለም ንጉሴ ገለጹ፡፡

“ህብረብሔራዊ ወንድማማችነትና እህትማማችነት ለዘላቂ ሰላምና ሁለንተናዊ ብልፅግና” በሚል መሪ ሃሳብ በአርባምንጭ ከተማ ህዝባዊ ውይይት ተካሄዷል፡፡

በውይይቱ ወ/ሮ አይናለም ንጉሴ ÷ የኑሮ ውድነትን ለማቃለል ምርትና ምርታማነት በመጨመር በቁርጠኝነት መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።

የከተማዋን ዕድገት ለማፋጠን ርብርብ እንደሚያስፈልግ በመግለጽ ባለድርሻ አካላትም የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት አለባቸው ብለዋል፡፡

በከተማው የሚሠሩ መሠረተ ልማቶች በጊዜ እንዲጠናቀቁ ገቢ መሰብሰብ ላይ በትኩረት መሰራት እንዳለበት ጠቅሰው ÷ ወንድማማችነት መገንባት ላይና የኑሮ ውድነትን የማቃለል አማራጮችን አሟጦ መጠቀም እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡

የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ አባል አቶ ሳዳት ነሻ ÷ በጥረታችን የኢትዮጵያን ብልፅግና ለማረጋገጥ የሚጠበቅብንን ኃላፊነት እንወጣለን ብለዋል፡፡

የጋሞ ህዝብ የሰላም ተምሳሌት እንደመሆኑ መጠን ሰላሙን አስጠብቆ መቀጠል እንዳለበትም ነው ያነሱት፡፡

የአርባምንጭ ከተማ ከንቲባ ገዛኸኝ ጋሞ በበኩላቸው ÷ ከተማዋ በኢትዮጵያ ካሉ የቱሪስት መዳረሻ ከተሞች አንዷ መሆኗን ተናግረዋል።

በመድረኩ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የፓርቲና መንግስት አመራሮች እንዲሁም የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪዎች እንደተሳተፉ የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡