የሀገር ውስጥ ዜና

የተለያዩ ሀገራት መሪዎች አዲስ አበባ ገቡ

By Melaku Gedif

February 16, 2024

አዲስ አበባ፣ የካቲት 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በ37ኛው የአፍሪካ ኀብረት የመሪዎች ጉባዔ ላይ ለመሳተፍ የተለያዩ ሀገራት መሪዎች አዲስ አበባ ገብተዋል።

የስዋቲኒ ጠቅላይ ሚኒስትር ሩሴል ዲላሚኒ በጉባኤው ለመሳተፍ ማምሻውን ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የስራ እና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል አቀባበል አድርገውላቸዋል።

እንዲሁም የቻድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሱክሴ ማስራ ማምሻውን ቦሌ አለምአቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የሰላም ሚኒስትር አቶ ብናልፍ አንዱዓለም አቀባበል አድርገውላቸዋል።

የሴራሊዮን ምክትል ፕሬዝዳንት መሀመድ ዡሌ ዣሎህ በጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ማምሻውን አዲስ አበባ ገብተዋል።

ቦሌ አለምአቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የማዕድን ሚኒስትር ኢንጅነር ሀብታሙ ተገኝ አቀባበል እንዳደረጉላቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል።

በመራኦል ከድር