የሀገር ውስጥ ዜና

በ37ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ 49 ሀገራት እንደሚሳተፉ ተገለጸ

By Amele Demsew

February 16, 2024

አዲስ አበባ፣ የካቲት 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በ37ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ እስካሁን 49 ሀገራት እንደሚሳተፉ ማረጋገጣቸውን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ፡፡

የአገልግሎቱ ሚኒስትር ዴዔታ ሰላማዊት ካሳ በሰጡት መግለጫ÷ በ37ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ የሚሳተፉ እንግዶች አዲስ አበባ እየገቡ ነው ብለዋል፡፡

እስካሁን ድረስም 49 ሀገራት በመሪዎቻቸው እና በተወካዮቻቸው በኩል በጉባዔው እንደሚሳተፉ ማረጋገጣቸውን ነው የገለጹት፡፡

ከዚህም ውስጥ 30 የሀገራት ፕሬዚዳንቶች እና ስድስት ምክትል ፕሬዚዳንቶች እንደሚገኙ ጠቅሰዋል፡፡

በጉባዔው ከአፍሪካ ሀገራት በተጨማሪ ሌሎች ሀገራት በመሪዎች እና በተወካዮቻቸው በኩል እንደሚሳተፉ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ጨምሮ የ13 ዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎች በጉባኤው ይሳተፋሉ ብለዋል፡:

ኢትዮጵያ በባለብዙ ዲፕሎማሲ መድረክ ላይ የሠላም ፣ የአንድነት እና የነጻነት አርማ ሆና መቆየቷን አንስተዋል ሚኒስትር ዴዔታዋ፡፡

ይህም ኢትዮጵያ የሁሉም አፍሪካዊ ቤት ናት የሚውን ሃሳብ የሚያረጋግጥ መሆኑን ጠቁመው ÷በመድረኩ ኢትዮጵያ የራሷን ሃሳብ እንደምታንጸባርቅ ገልጸዋል፡፡

ከዋናው ስብሰባ በተጓዳኝ በኢትዮጵያ አዘጋጅነት ሁለት ትልልቅ ጉባዔዎች እደሚካሄዱም አንስተዋል፡፡

እነዚህም “የዲጂታላይዜሽን መስፋፋት ለአፍሪካ ትራንስፎርሜሽን እና የአፍሪካ የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ “በሚል መሪ ሃሳብ የሚካሄዱ ናቸው ብለዋል፡፡

የካቲት 9 እና 10 ቀን 2016 ዓ.ም በዓድዋ ድል መታሰቢያ በሚካሄዱት ሁለቱ ጉባዔዎች የሀገራት መሪዎች እና የዓለም አቀፍ ተቋማት ሃላፊዎች እንደሚሳተፉ ጠቁመዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ