የሀገር ውስጥ ዜና

ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ለ14 የአፍሪካ ሀገራት ቀዳማዊ እመቤቶች አቀባበል አደረጉ

By Melaku Gedif

February 17, 2024

አዲስ አበባ፣ የካቲት 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) 14 የአፍሪካ ሀገራት ቀዳማዊ እመቤቶች በ28ኛው የአፍሪካ ቀዳማዊ እመቤቶች የልማት ድርጅት መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ለመሳተፍ አዲስ አበባ ገብተዋል፡፡

ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው በጉባዔው ለመሳተፍ ወደ ኢትዮጵያ ለመጡ 14 የአፍሪካ ሀገራት ቀዳማዊ እመቤቶች አቀባበል አድርገዋል፡፡

በአቀባበል ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ለ14 የአፍሪካ ሀገራት ቀዳማዊ እመቤቶች እና ጥሪ ለተደረገላቸው እንግዶች የምሳ ግብዣ ተደርጓል፡፡

በተጨማሪም የኢትዮጵያን ባህላዊ ቁሳቁስ፣ አልባሳት፣ ጌጣጌጦች፣ የተለያዩ የባህል ምግቦች እንዲሁም ባህላዊ እሴቶችን የሚያስተዋውቅ ኤግዚቢሽን ለዕይታ መቅረቡ ተመላክቷል፡፡

28ኛው የአፍሪካ ቀዳማዊ እመቤቶች የልማት ድርጅት መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ ”በአህጉሩ ተገቢ የትምህርትና የጤና ተደራሽነት ለሴቶች እና ልጃገረዶች” በሚል መሪ ሃሳብ ነገ ይካሄዳል፡፡

በፍሬሕይወት ሰፊው