የሀገር ውስጥ ዜና

የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና እንቅስቃሴ ውጤት እያስገኘ ነው- ዋምኬሌ ሜኔ

By Feven Bishaw

February 18, 2024

አዲስ አበባ፣ የካቲት 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አፍሪካውያኖች ምርቶቻቸውን ከሌሎች ጋር ከመገበያየት ይልቅ እርስ በራስ በስፋት ወደ መገበያየት ተሸጋግረዋል ሲሉ የአፍሪካ ነፃ ንግድ ፀሐፊ ዋምኬሌ ሜኔ ተናግረዋል።

የተቋሙን አፈፃፀም አስመልክተው መግለጫ የሰጡት ፀሐፊው የነፃ ንግድ ገበያ ዞን ስራ ላይ ከዋለበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን አንስተዋል።

በተለይም ሀገራት፣ መንግስታዊና የግል ተቋማት እንዲሁም ወጣቶች ይህን ተረድተው እንዲሳተፉ በማድረግ በኩል የተሰሩ ስራዎች ሰፊ ጊዜ የወሰዱ ነገር ግን ጥሩ ውጤት የታየባቸው መሆኑን አመላክተዋል።

የነፃ ንግድ ዞን ዓላማ አፍሪካን ወደ የገበያ ማዕከል ማምጣት ነው ያሉት ፀሐፊው ባለፉት ዓመታት በ 7 ሀገራት የተጀመረው የንግድ ልውውጥ ወደ 35 ሀገራት ከፍ ብሏል ነው ያሉት።

እስካሁን በተሰሩ ስራዎች ጉድለቶች እና ተግዳሮቶች ያሉ ቢሆንም ተጨባጭ ለውጦች ተመዝግቧል ሲሉ ተናግረዋል።

ከ2063 አጀንዳ ጋር ተያይዞ ሲገመገም በጥሩ መንገድ ያለ መሆኑን ለመረዳት እንደሚያስችልም ፀሐፊው አመላክተዋል።

በመራኦል ከድር