አዲስ አበባ፣ የካቲት 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) 37ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ እና 44ኛው የአስፈፃሚዎች ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ በስኬት መጠናቀቁን የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል አስታውቋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማን ሰላምና ደህንነት የበለጠ ለማጠናከር፣ የትራፊክ ፍሰቱን የተሳለጠ ለማድረግ ግብረ-ኃይሉ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት፣ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ከአፍሪካ ህብረት ጽ/ቤት ጋር በትብብር በመስራቱ ለተገኘው ስኬት ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል ብሏል መግለጫው።
ለጉባኤው የመጡ እንግዶች በአዲስ አበባ ሲንቀሳቀሱ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ እጀባና ጥበቃ ማድረጉን የገለፀው የጋራ ግብረ-ኃይሉ÷ መሪዎች ወደ ሀገራቸው እየተመለሱ እንደሆነ ጠቁሟል።
በግብረ-ኃይሉ የተሠራው ፀጥታ የማስከበር ተግባር አፍሪካን ሊወክል እና ሊያኮራ የሚችል በመሆኑ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ኅብረትን ለማጠናከር ያላትን ሚና እንዲሁም ቁርጠኝነት ያሳየ ነበርም ተብሏል፡፡
የአዲስ አበባ ነዋሪዎች እንግዶችን በክብር ከመቀበል ጀምሮ በየሆቴሎቹ ደረጃውን የጠበቀ መስተንግዶ በማድረግ፣ ከፀጥታ ኃይሉ የሚሰጠውን መመሪያ በቅንነት በመቀበል አጋርነታቸውን በማሳየታቸው የፀጥታና ደህንነት አመራሮችና አባላትም በጥብቅ ዲሲፕሊን እየተመሩ የተሰጣቸውን ኃላፊነት በመወጣታቸው ጉባኤው ያለምንም የፀጥታ ችግር በሰላምና በስኬት በመጠናቀቁ ግብረ-ኃይሉ አመስግኗል፡፡