አዲስ አበባ፣ የካቲት 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) መቀመጫውን በሶማሊያ ያደረገው የአልሸባብ የሽብር ቡድን የጋንታና የጦር መሪዎችን ጨምሮ 41 ግለሰቦች እስከ ዕድሜ ልክ በሚደርስ ጽኑ እስራት ተቀጡ።
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ድሬዳዋ ምድብ 4ኛ ወንጀል ጅግጅጋ ተዘዋዋሪ ችሎት ተከሳሾቹ በቀረበባቸው ክስ በአራት መዝገብ ጉዳያቸውን ሲመለከት ከቆየ በኋላ መርምሮ እስከ ዕድሜ ልክ በሚደርስ ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ወስኗል።
ተከሳሾቹ 1ኛ የአልሸባብ የሽብር ቡድን የጦር መሪ ነው የተባለው ሁሴን አልመድ በቅጽል ስሙ (ሁሴን ጋፕ)፣ 2ኛ የአልሸባብ የጋንታ መሪ ነው የተባለው ኢብራሂም ጂብሪል ኢብራሂም እንዲሁም ሆሽ አደም ኢብራሒም፣ ረሃዋ ኢብራሂም እና አሊ በሽርን ጨምሮ አጠቃላይ 41 ተከሳሾች ናቸው።
ተከሳሾቹ በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል መርማሪዎች ከክልሉ ፖሊስ ጋር በመሆን ምርመራ በማከናወን በሕዳር 5 ቀን 2015 ዓ.ም የጊዜ ቀጠሮ መዝገቡን ለዐቃቤ ሕግ አስረክበዋል።
የፍትሕ ሚኒስቴር የተደራጁ እና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጀነራል ዐቃቤ ሕግ በሕዳር 27 ቀን 2015 ዓ.ም በዋለው ችሎት የ57 የሰው ምስክሮችን የስም ዝርዝርና እና 396 ገጽ የሠነድ ማስረጃዎችን አካቶ የሽብር ወንጀል ክስ በተከሳሾቹ ላይ አቅርቧል።
ተከሳሾቹ መቀመጫውን ጎረቤት ሀገር ሶማሊያ ያደረገው የአልሸባብ ዓለም አቀፍ የሽብር ቡድን አባል በመሆን ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ ስልጠና በመውሰድ፣ ሕዝብን በማሸበር መንግስትን ለማስገደድ የተሰጣቸውን ተልኮ ተቀብለው በ2014 ዓ.ም መጨረሻ በሶማሌ ክልል አፍዴር ዞን ባሬይ፣ በጎዲጎድ፣ በቆህሌ፣ በሀርዱር እና በሃርጌሌ ወረዳዎች እንዲሁም በሸበሌ ዞን አዳድሌይ፣ በመስታኒል እና በፊርፊር ወረዳዎች በሚገኙ ቀበሌዎች በተከታታይ ጥቃት መፈጸማቸው በክሱ ተመላክቷል።
በተፈጸመው ጥቃት የ265 ዜጎችን ሕይወት በማጥፋት የ323 ንፁሃንን እና የክልሉ ልዩ ኃይል የፖሊስ አባላት እንዲሁም በአካባቢውን በሚጠብቁ ሚሊሻዎች ላይ ከከባድ እስከ ቀላል የአካል ጉዳት በማድረስ እንዲሁም ስድስት የሕዝብ ት/ቤቶችን፣ የመንግስት የመሰረተ ልማቶችን፣ የግለሰብ ንብረቶች፣ ተሽከርካሪዎችን ጨምሮ 13 ሚሊየን 550 ሺህ ብር የሚገመቱ ንብረቶችን አውድመዋል ሲል ዐቃቤ ሕግ በክሱ ዘርዝሯል።
በተጨማሪም ተከሳሾቹ ሁለት የጭነት ተሽከርካሪዎችን፣ 470 ፍየልና በጎችን፣ 119 ግመሎችን ከማህበረሰቡ ዘርፈው መውሰዳቸው በክሱ ተመላክቷል።
በዚህ መልኩ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 23/1 ሀ እና ለ አንቀጽ 35 እንዲሁም ሽብርተኝነትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 1176/2012 አንቀጽ 3(2) በመተላለፍ በዋና ወንጀል አድራጊነት የሽብር ወንጀል ክስ ቀርቦባቸዋል፡፡
በሁለተኛው ክስ ደግሞ የሽብር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 1176/2012 አንቀጽ 30 ንዑስ አንቀጽ 1 ስር የተደነገገውን ድንጋጌ በመተላለፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሽብርተኝነት የተፈረጀው አልሸባብ የሽብር ቡድን ድርጅት መሆኑን እያወቁ አባል በመሆን የወንጀል ክስ ቀርቦባቸዋል።
ተከሳሾቹ ክሱ ከደረሳቸው በኋላ ጠበቃ የማቆም አቅም እንደሌላቸው ለችሎቱ መግለጻቸውን ተከትሎ ችሎቱ የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ከተከላካይ ጽ/ቤት የመንግስት ተከላካይ ጠበቃ እንዲመደብላቸው ትዕዛዝ ሰጥቷል።
ጥር 5 ቀን 2015 ዓ.ም በነበረ ቀጠሮ በችሎት የክስ ዝርዝሩ በንባብ ከተሰማ በኋላ ተከሳሾቹ የዕምነት ክህደት ቃላቸውን አስመዝግበዋል።
ከሳሽ ዐቃቤ ሕግ ለወንጀሉ መፈጸም የሚያስረዱ የሰነድ ማስረጃዎችንና የሰው ምስክሮችን በተለያዩ ቀናት አቅርቦ አሰምቷል።
ፍርድ ቤቱም የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን መርምሮ ተከሳሾቹ በተከሰሱበት ድንጋጌ እንዲከላከሉ ብይን የሰጠ ቢሆንም÷ ተከሳሾች በአምስት ቀጠሮዎች የመከላከያ ማስረጃ ማቅረብ ባለመቻላቸው ምክንያት የመከላከያ ማስረጃ የማቅረብ መብታቸው ታልፎ እያንዳንዳቸው የጥፋተኝነት ፍርድ ተላልፎባቸዋል።
ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኝ የቅጣት አስተያየትን ከግምት ውስጥ በማስገባት መርምሮ እያንዳንዳቸውን በጽኑ እስራት እንዲቀጡ ወስኗል።
በዚህም የአልሸባብ የሽብር ቡድን የጦር መሪ ነው የተባለው ሁሴን አልመድ በቅጽል ስሙ (ሁሴን ጋፕ) እና የአልሸባብ የጋንታ መሪ ነው የተባለው ኢብራሂም ጂብሪል ኢብራሂም ጥፋተኛ በተባሉበት ድንጋጌ በዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ተወስኗል።
በእነ ሆሽ አደም ኢብራሒም መዝገብ የተካተቱ 19 ተከሳሾች በ11 እና በ12 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ተወስኗል።
ለአልሸባብ የሽብር ቡድን የጦር መሳሪያ ሲያቀርቡ ነበር የተባሉ በነ ረሃዋ ኢብራሂም መዝገብ የተካተቱ 8 ተከሳሾችን በሚመለከት ደግሞ በየደረጃው በ8 እና በ9 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ውሳኔ ተላልፏል፡፡
ሌሎች በእነ አሊ በሽር መዝገብ የተካተቱ 10 ተከሳሾችን ደግሞ በየደረጃው በ7 ዓመት ከ8 ወራት ጽኑ እስራትና በ8 ዓመት ከ6 ወራት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ተወስኗል።
በእነ ሆሽ አደም ኢብራሒም መዝገብ በተራ ቁጥር 15 እና 21ኛ የተጠቀሱ ሁለት ተከሳሾችን ግን የሽብር ቡድኑ አባል በመሆን ብቻ በ2 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ሰጥቷል።
በታሪክ አዱኛ